ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 19 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ምዕራፍ 19 1 ነገሥታትንና መኳንንትን፥ ታላላቆችንና ክቡራንንም፥ የተዋቡ ሴቶችንና መልካማ ቆነጃጅትንም የሰበሰብሻቸው ምድር ሆይ፥ ከአንቺ የተነሣ ወዮ! 2 ደም ግባት ያላቸውን፥ ባተ መልካሞች የሆኑትን፥ ዕውቀትና ልቡናም ያላቸውን፥ ቃላቸውም እንደምታንጐራጕር በገና፥ እንደ ክራርና እንደ መሰንቆም አመታት ያማረ ቃል ያላቸውን፥ 3 እንደ ጣፋጭ የወይን መጠጥም ደስ የሚያሰኝ ዜማ ያላቸውን፥ ዐይኖቻቸውም እንደ አጥቢያ ኮከብ የሚያበሩትን፥ 4 ቀኝ እጃቸውም እንደሚሰጥና እንደሚነሣ ጽኑዕ የሆነላቸውን፥ የሚነድፉ፥ እግሮቻቸውም ለማየት ያማሩና እንደተስተካከሉ መንኰራኩሮች የሚሮጡ ኀያላን ሰዎችን የሰበሰብሻቸው ምድር ሆይ፥ ከአንቺ የተነሣ ወዮ! 5 በእግዚአብሔር ፈቃድ ተልከሃልና የመልከ መልካም ሰዎችን ነፍሳት ከሥጋቸው የለየህ ሞት ሆይ! ከአንተ የተነሣ ወዮ! 6 አንችም ምድር! እግዚአብሔር ከአንቺ ያስገኛቸውንና ወደ አንቺ የመለሳቸውን ብዙዎች ሥጋዎችን ሰብስበሻልና ከአንቺ የተነሣ ወዮ! በፈቃደ እግዚአብሔር ከአንቺ ወጣን፤ ወደ አንቺም እንመለሳለን፤ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በአንቺ ላይ ደስ አለን። 7 ለሬሳዎቻችን ምንጣፍ ሆንሽ፤ በላይሽ ተመላለስን፤ በውስጥሽም ተኛን፤ ፍሬሽን በላን፤ አንቺም ሥጋችንን በላሽ። 8 ከምንጭሽም ውኃ ጠጣን፤ አንቺም ከደማችን ምንጭ ጠጣሽ፤ ከመሬትሽ ስባት በላን፤ አንቺም የአጥንቶቻችንን ስባት በላሽ። 9 ምግባችን ልትሆኝ እግዚአብሔር እንዳዘዘሽ ያማረ ጠል ከአለው ከመሬትሽ እህልን በላን፤ አንቺም የሥጋችንን ደም ግባት ተቀበልሽ፤ እግዚአብሔርም እንዳዘዘሽ ለምግብሽ ትቢያን አደረግሽው። 10 ብዙዎች ኀያላን ነገሥታትንና መኳንንትን የሰበሰብህ፥ የፈጠራቸው እግዚአብሔርም እንዳዘዘህ ከገናናነታቸውና ከግርማቸው የተነሣ ያልፈራህ፥ ጦም አዳሪውንም ያልናቅህ ሞት ሆይ! ከአንተ የተነሣ ወዮ! 11 መልካቸውም ለአማረ ሰዎች አልራራህም፤ ኀይለኞችንና አርበኞችንም አልተውህም፤ ባለጸጎችንና ድሆችን፥ መልከ ክፉዎችንና መልከ መልካሞችን፥ ሽማግሌዎችንና ልጆችን፥ ሴቶችንና ወንዶችንም አልተውህም። 12 በጎ የሚያስቡትንና ከትእዛዙ ያልተላለፉትንም አልተውህም፤ በሥራቸውም እንደ እንስሳ የሆኑ ክፉ ነገር የሚያስቡትንም አልተውህም። በመልካቸው ደም ግባት፥ በቃላቸውና በነገራቸው ጣዕም ፍጹማን የሆኑትን አልተውህም። 13 ቃላቸው ቁጡ የሆነና አፋቸውም ርግማንን የተመላ ሰዎችን አልተውህም፤ ነፍሶቻቸውንም በብርሃንና በጨለማ መዛግብትህ ሰበሰብህ። 14 ምድርም መለከት እስከሚነፋበትና ሙታን እስከሚነሡበት ጊዜ ድረስ በዋሻም ቢሆን፥ በመሬትም ቢሆን ሥጋቸውን ሰበሰበች። 15 ክፉ አድራጊዎች እንደ ሠሩት ሥራቸው ዋጋቸውን ይቀበላሉ፤ በመለከት ድምፅና በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሙታን እንደ ዐይን ጥቅሻ ይነሣሉና፥ በጎ ሥራ የሠሩም ደስ ይላቸዋል። |