ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 16 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በሥጋህ፥ በእጅህና በእግርህ ጥፍር፥ በራስህም ጠጕር ያለውን እስኪ አንተ ራስህ አስበው፤ በቈረጥሃቸው ጊዜ ፈጥነው ይወጣሉና፥ ለማመን ልብና አእምሮ ከአለህ በዚህ ዕወቅ። 2 እነዚህ የእጅህና የእግርህ ጥፍር፥ የራስም ጠጕር ከወዴት ይወጣሉ ትላለህ? ከሞት እንደምትነሣ ታውቅ ዘንድ በሌላ ሥጋ ያይደለ በአንተ ሥጋ የሚደረግ ትንሣኤን እንድታውቅ ይበቅሉ ዘንድ እግዚአብሔር ያዘጋጀው አይደለምን? 3 አንተም የሙታን ትንሣኤ የለም እያልህ ሕዝቡን ስለአሳትህ ኀጢአትንና በደልን እንደ ሠራህ በሙታን ትንሣኤ ጊዜ ፍዳህን ትቀበላለህ። 4 አሁንም የፍዳህ ቀን በደረሰችብህ ጊዜ ታያታለህ፤ ስንዴም ቢሆን፥ ገብስም ቢሆን አንተ ስንኳ የዘራኸው ይበቅል ዘንድ እንቢ አይልምና። 5 ዳግመኛም አንተ የተከልኸው ተክል አልበቅልም አይልም፤ የወይን ተክልም ቢሆን፥ የበለስ ተክልም ቢሆን ቅጠሉና ፍሬው አይለወጥም። 6 ወይን ብትተክልም በለስ ይሆን ዘንድ አይለወጥም፤ በለስም ብትተክል ወይን ይሆን ዘንድ አይለወጥም፤ ስንዴም ብትዘራ ገብስ ይሆን ዘንድ አይለወጥም፤ 7 ገብስም ብትዘራ ስንዴ ይሆን ዘንድ አይለወጥም። ነገር ግን ሁሉ በየዘሩና በየወገኑ፥ በየፍሬውና በየእንጨቱ፥ በየቅጠሉና በየሥሩ፥ ከእግዚአብሔር በሚገኝ የምሕረት ጠል በረከትን ተቀብሎ ፍሬን ያወጣል። 8 እንደዚሁም ምድር እግዚአብሔር እንደ ዘራባት ነፍስንና ሥጋን ታስገኛለች፤ እግዚአብሔር የዘራቸው ሥጋና ነፍስ ተዋሕደው ይነሣሉ እንጂ በጎ ሥራ የሠሩ ሰዎች ክፉ ሥራ በሠሩ ሰዎች አይለወጡም፤ ክፉ ሥራም የሠሩ ሰዎች በጎ ሥራን በሠሩ ሰዎች አይለወጡም። 9 መለከት የሚነፋበትም ሰዓት በደረሰ ጊዜ ሙታን ከእግዚአብሔር በሚገኝ የጠል ምሕረት ይነሣሉ፤ በጎ ሥራ የሠሩ ሰዎች የሕይወት ትንሣኤን ይነሣሉ፤ ዋጋቸውም እግዚአብሔር ለደጋጎች ያዘጋጀው፥ መከራና ደዌ የሌለበት፥ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ የማይሞቱበት የንጹሓን ማደሪያ የደስታ ገነት ነው። 10 ክፉ ሥራ የሠሩ ግን የደይን ትንሣኤ ተነሥተው ከአሳታቸው ከዲያብሎስ ጋራ፥ 11 ከሰው ልጆች ሁሉ አንድ ሰው ስንኳ ይድን ዘንድ ከማይወዱ ከሠራዊቶቹ ከአጋንንትም ጋራ ወደ ዘለዓለም ቅጣት ይሄዳሉ፤ 12 የጨለማ ዳርቻ ወደ ሆነ፥ ጥርስ ማፋጨትና ልቅሶ ወዳለበት፥ ይቅርታና ምሕረት ወደሌለበት፥ እስከ ዘለዓለም ድረስ መውጫ ወደሌለበት ወደ ገሃነም ይወርዳሉ። በሥጋቸው ሳሉ በምድር ላይ በሕይወታቸው በጎ ሥራ አልሠሩምና። 13 ስለዚህም ነፍስና ሥጋ በትንሣኤ ጊዜ ይፈረድባቸዋል። 14 እግዚአብሔር የተአምራቱን ብዛት የሚያሳይባት የነፍስና የሥጋን በአንድነት መነሣት ለማያምኑ ሰዎች ወዮላቸው! 15 ሁሉም እያንዳንዱ እንደ ሥራውና እንደ እጁ ድካም ዋጋውን ይቀበላል። |