ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በጎ ሥራቸውን ያገኙ ያንጊዜ ደስ ይላቸዋል፤ ሙታን አይነሡም እያሉ ቸል ያሉ ግን ሙታን ከማይጠቅም ክፉ ሥራቸው ጋራ እንደ ተነሡ በአዩ ጊዜ ያንጊዜ ያዝናሉ። 2 ያም የሠሩት ሥራቸው ይፈርድባቸዋል፤ የሚከራከራቸውም ሳይኖር እንደሚፈረድባቸው እነርሱ ራሳቸው ያውቃሉ። 3 በልቅሶና በፍርድ ቀን በቍርጥ ፍርድ ቀንና በእግዚአብሔር ቀን ዝንጉዎች በሚቆሙበት ቦታ ይቆማሉ። 4 በፍጹም ጨለማ ቀን፥ በጉም ቀን፥ በብልጭልጭታ ቀን፥ በመብረቅ ቀን፥ 5 በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ቀን፥ በብርድና በሙቀት ቀን፥ በውርጭም ቀን፥ 6 ክፉ ሰው ክፋትን እንደ ሠራ ፍዳን በሚቀበልባት ቀን፥ ንጹሕ ሰውም ንጹሕ ሥራን እንደ ሠራ ዋጋውን በሚቀበልባት ቀን፥ ኀጢአተኛም ኀጢአትን እንደ ሠራ ፍዳውን እንደሚቀበል፥ 7 ጌታም ከባርያው በማይከብርባት ቀን፥ እመቤትም ከባርያዋ በማትከብርበት ጊዜ፥ 8 ንጉሡም ከድሃው በማይከብርበት ጊዜ፥ ሽማግሌውም ከሕፃኑ በማይከብርበት ጊዜ፥ አባት ከልጁ በማይከብርበት ጊዜ፥ እናትም ከልጅዋ በማትከብርበት ጊዜ፥ 9 ባለጸጋው ከድሃው በማይከብርበት ጊዜ፥ ትዕቢተኛም ከተዋረደው ሰው በማይከብርበት ጊዜ፥ ታላቁም ከታናሹ በማይከብርበት ጊዜ፥ የፍርድ ቀን ናትና፥ የፍዳና የቅጣት ቀን ናትና፥ ሁሉም እንደ ሠራው የሚቀበልባት ቀን ናትና። 10 በጎ ሥራ የሠሩም ዋጋቸውን የሚቀበሉባት ቀን ናትና፥ ክፉ የሠሩም ክፉውን የሚቀበሉባት ቀን ናትና። 11 ዋጋቸውን ያገኙም ደስ የሚሰኙባት ቀን ናትና፥ ክፉውንም የተቀበሉ የሚያዝኑባት ቀን ናትና። ሙታን አይነሡም እያሉ መጻሕፍትን የሚያሳብሉትም ያያሉ። 12 ያንጊዜም የምድር ኃጥኣን ስለ ሠሩት ኀጢአታቸውና በምድር ሳሉ መልካም ባለማድረጋቸው ስለሚያገኛቸው መረጋጋት ስለሌለው ኀዘናቸው ያለቅሳሉ። 13 እንደዚሁም በምድር ላይ ሳሉ በጎ ሥራን ሠርተዋልና በጎ ሥራን የሠሩ የደጋጎች ደስታ እስከ ዘለዓለም ድረስ አይፈጸምም። 14 ከሞትም እንደሚነሡ አውቀዋልና ከፈጣሪያቸው ሕግ አልወጡም። 15 ከትእዛዙም ስላልወጡ ሁለት ሕይወትን ይወርሳሉ፤ በምድርም ላይ ዘራቸውን አበዛ፤ ልጆቻቸውንም ባረካቸው። 16 በሰማያትም በትንሣኤ ቀን ባለጸጎች በሚደኸዩበት ጊዜ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳቸዋል። 17 ክፉ የሚሠሩና የሙታንን መነሣት የማያምኑ፥ የእግዚአብሔርን ሕግና የትንሣኤንም ቀን የማያስቡ ያለቅሳሉ። 18 ያንጊዜም መጨረሻ የሌላት፥ ድኅነትና መረጋጋት የሌለባት የምታገኛቸውን መከራ ያያሉ፤ በልቡናቸውም መረጋጋትና ዕረፍት የሌለው ኀዘን ይሆናል። 19 የማያንቀላፋ ትል፥ የማይጠፋም እሳት ያገኛቸዋል። 20 ሥጋቸውም ባለበት ቦታ እሳትና ድኝ፥ ጥቅል ነፋስ፥ ውርጭና በረድ፥ ቀቅም በላያቸው ይዘንማል። 21 የሙታንንም መነሣት በማያምኑ ሰዎች ላይ ገሃነመ እሳት አለባቸው። |