ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 14 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የአይሁድና የሳምራውያን፥ የፈሪሳውያንና የሙታንን ትንሣኤ የማያምኑ የሰዱቃውያን ነገር እኔን እጅግ ያሳዝነኛል፤ ልቡናዬም ያውቀዋል። አይሁድ፦ እንብላ፤ እንጠጣም፤ ነገም እንሞታለን፤ በዚያም የምናየው የለም ይላሉ። 2 ሳምራውያን ግን ሥጋችን ትቢያ ይሆናልና አይነሣም ይላሉ። 3 ትንሣኤም በተደረገ ጊዜ የነፍሳችንን መነሣት እናምናለን። ነፍስ እንደ ነፋስ የማትታይና እንደ ነጐድጓድ ድምፅ ስለ ሆነች እነሆ እዚህ አለች የማይሏትና የማትታይ ስለ ሆነች ሥጋ ቢሞት አትሞትምና። 4 ሥጋችን ግን በሁሉ ትታያለች፤ ዐመድና ትቢያም ትሆናለች። አውሬዎች ይበሏታልና፥ ትሎችም በመቃብር ይበሏታልና። 5 እነዚያም የበሏት እንደ ሣር ይሆናሉና፥ እንዳልተፈጠሩም ትቢያ ይሆናሉና ዐመድ ይሆናሉ፤ ፍለጋቸውም አይገኝም። የፈረሱ ሥጋዎች የት ይገኛሉ? 6 ፈሪሳውያንም እንዲህ ይላሉ፥ “የሙታንን መነሣት እናምናለን፤ ነገር ግን ነፍሳትን በምድር ያይደለ በሰማያት ሌላ ሥጋ ያለብሳቸዋል።” 7 ሰዱቃውያንም እንዲህ ይላሉ፥ “ነፍሳችን ከሥጋችን ከወጣች በኋላ ከሞት አንነሣም፤ ለነፍስና ለሥጋም ትንሣኤ የላቸውም፤ ከሞትንም በኋላ አንነሣም።” 8 ስለዚህም እጅግ ፈጽመው ይስታሉ፤ በእግዚአብሔርና በጌትነቱም ላይ ጽርፈትን ይናገራሉና የእነርሱ ነገር ያሳዝነኛል። 9 የሚያጸድቃቸው እግዚአብሔርንም አላመኑትምና ለመዳን ተስፋ የላቸውም፤ ለመዳንና ከሙታን ለመነሣትም ተስፋ የላቸውም። 10 አንተ ዕውር አይሁዳዊ ካለመኖር የፈጠረህን፥ እንደ ምራቅም ስትሆን ሰው ያደረገህን እግዚአብሔርን አላዋቂ ታደርገዋለህን? በምሳሌውና በመልኩ የፈጠረህ ነፍስህንና ሥጋህን አዋሕዶ ማስነሣት ይሳነዋልን? 11 ከእግዚአብሔር እጅ አታመልጥምና እንደዚህ አታስብ፤ ሳትወድ ትነሣለህ፤ በሞትህም ጊዜ የተያዝህባት የሲኦል ገመድ በአንገትህ አለችና ሳትወድ ይፈረድብሃል። 12 በአንገትህ የታሠረች ያች ገመድም በእናትህ ማኅፀን ከሲኦል ግንድ ለአንተ ትበቅላለችና። አንተም ባደግህ ጊዜ እርሷም ታድጋለችና። 13 አንተም በሞትህ ጊዜ በአንገትህ ያኖሯታል፤ ግንዷንም በሳቧት ጊዜ እርስዋ ታመጣቸዋለች፤ ቅርንጫፎችዋንም ትስባለች። 14 ኃጥኣን ሁሉ በአንገታቸው ገመድ እንዳለ በውስጧ ተይዘው አሉና። 15 የኃጥኣንም ነፍሳት ሁሉ ከአሉበት ከሰማይ ዳርቻ ይመጣሉ፤ እንደዚሁም ገመድህ ነፍስህን ካለህበት ስባ አምጥታ ወደ ሲኦል ታገባሃለች። 16 ሥጋህም ከነፍስህ ከተለየ በኋላ እንደ አባታችን እንደ አዳም ሥጋ ፍጹም ሆኖ በእግዚአብሔር በቸርነቱ ጠል ይነሣል። በዚያም በደልንና ኀጢአትን እንደ ሠራህ እንደ አለማመንህ ፍዳህን ትቀበላለህ። 17 ሌላውን ብቻ የምታስት አይምሰልህ፤ ራስህም ትስታለህ፥ በስሕተትህም በመቃብር ትኖራለህ፤ ከእግዚአብሔርም ትእዛዝ ወጥተው ይስቱ ዘንድ የሙታን ትንሣኤ የለም ትላለህ። 18 እንደ ሠራኸው ሥራህ ፍዳህን ይሰጥህ ዘንድ ያስነሣሃል እንጂ በትቢያና በዐመድ ውስጥ ማን ይተውሃል? 19 ያንጊዜ ግን በነፋስ ውስጥ ያለ ነፋስ ባሕርይህም ቢሆን፥ በውኃ ውስጥ ያለ ውኃ ባሕርይህም ቢሆን፤ በመሬት ያለ መሬት ባሕርይህም ቢሆን፥ በእሳትም ውስጥ ያለ እሳት ባሕርይህም ቢሆን ይመጣል። 20 በአንተ ያደረች፥ በጨለማ ቦታ የምትኖር ነፍስም ብትሆን ትመጣለች። 21 በገነት በደስታ የሚኖሩ የጻድቃን ነፍሳትም ይመጣሉ። 22 አንተም አይሁዳዊ፥ አንተም ሳምራዊ፥ አንተም ፈሪሳዊ፥ አንተም ሰዱቃዊ እስኪፈረድብህ ድረስ በጨለማ ትኖራለህ። 23 ያንጊዜም ሰውን ስለ አሳትህ እንደ ሥራህ እግዚአብሔር እንደሚከፍልህ ታያለህ። 24 እንዲህም ትላቸዋለህ፦ የሞቱ ሰዎች አይነሡም፤ ነገ እንሞታለንና እንብላ፤ እንጠጣም፤ በሙሴም ወንበር ተቀምጠህ በቃልህ የሙታን ትንሣኤ የለም ትላለህ። 25 ስለዚህም የኦሪትን መጽሐፍ እያወቅህ፥ የመጻሕፍትንም ቃል እያስተማርህ ሳትህ፤ ሰውን ከምታስት ሳትማር በቀረህ ይሻል ነበር። 26 በክፉ ትምህርትህና በማይጠቅም ቃልህ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከምታስክድ የመጻሕፍትን ቃል በአላወቅህ ይሻልህ ነበር። 27 አንተ ግን እንደ ሥራህና እንደ ከንፈርህ ፍሬ ይሰጥሃል፤ እግዚአብሔር ፊት አይቶ አያዳላምና፥ በጎ ሥራንም ለሚያስተምሩ ለወዳጆቹ ከአዘጋጀው ጸጋ ይሰጣቸዋልና። 28 አንተም ከሚፈረድብህ ከእግዚአብሔር እጅ የምታመልጥበት የለም፤ እንደ ሥራህም ይከፍልህ ዘንድ አለው፤ አንተና ያስተማርሃቸውም በአንድነት ይፈረድባችኋል። 29 ሙታን እንደሚነሡም ዕወቅ፤ ሕጉን የጠበቁ ቢሆኑም ይነሣሉ፤ በመቃብር መቈየት አይችሉም፤ ዝናም በዘነመ ጊዜ ምድር ሣርን እንደምታወጣ ትእዛዙ ያወጣቸዋልና። 30 ዝናም ምድርን ባጠገባት ጊዜ ርጥብ እንጨት ቅጠልን እንደምታወጣ፥ ስንዴም ፍሬን እንደምታፈራ፥ እህልም ዝርዝርን እንደምታስገኝ፥ እግዚአብሔርም ከወደደ ፍሬዋን ትከለክል ዘንድ እንደማትችል፥ 31 የፀነሰችም ሴት ምጥ በያዛት ጊዜ ማኅፀኗን መዝጋት፥ ሳትወልድም ማምለጥ እንደማትችል። 32 ምድርም እንደዚሁ በእርስዋ የተሰበሰቡትን ታወጣለች፤ የእግዚአብሔርንም ቃል ከሰማች በኋላ ማኅፀንዋን መዝጋት አትችልም፥ ነገር ግን ከእግዚአብሔር የታዘዘ ጠል ወደ እርስዋ ይወርዳልና በአንድ ጊዜ ትወልዳቸዋለች። 33 ሥጋዎችም ሬሳዎቻቸው በወደቁባቸው ቦታዎች ይሰበሰባሉ፤ የነፍሳት መዛግብት ቤቶችም ይከፈታሉ፤ ነፍሳትም ቀድሞ ወደ ተለዩበት ወደ ሥጋ ይመለሳሉ። 34 መለከትም በተነፋ ጊዜ ሙታን እንደ ዐይን ጥቅሻ ይነሣሉ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ይቆማሉ፥ እንደ እጃቸውም ሥራ ይሰጣቸዋል። 35 ያንጊዜም ከሙታን ጋራ እንደምትነሣ ታያለህ፤ በምድር ላይ የሠራኸውንም ሥራ ሁሉ ታደንቃለህ፤ በዐይኖችህም ፊት ተጽፈው ባየሃቸው ጊዜ ያንጊዜ የማይረባ ጸጸትን ትጸጸታለህ። 36 ከሙታን ጋራም እንደምትነሣ፥ እንደ ሠራኸውም ሥራ እንደምትቀበል ታውቃለህ። |