ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 13 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የአመኑ እሊያ አምስቱ የመቃቢስ ልጆች ግን ለጣዖት የተሠዋውን መሥዋዕት መብላትን እንቢ ብለው ሰውነታቸውን ለሞት ሰጡ። 2 ይህ ዓለም እንደሚያረጅና እንደሚያልፍ፥ ተድላውም ለዘለዓለም እንደማይኖር ዐውቀው በሰማይ ከአለው እሳት ይድኑ ዘንድ ሰውነታቸውን ለእሳት ሰጡ። 3 ሰውን ከመገዳደር እግዚአብሔርን መገዳደር እንደሚከፋ፥ ከንጉሥም ቍጣ የእግዚአብሔር ቍጣ እንደሚከፋ አውቀዋልና። 4 “አቤቱ፥ በምድር ላይ ብዙ ዘመን ከመኖር በገነት አንዲት ቀን ደስ መሰኘት ይሻላል፤ ከብዙ ዘመኖችም የአንዲት ሰዓት ይቅርታህ ይሻላል፤ 5 የእኛ የሰዎች ዘመናችን ምንድን ነው? እንደ ጥላ የሚያልፍ፥ በእሳት ዳርም እንደ አለ ሰም አይደለምን? 6 አቤቱ አንተ ግን ለዘለዓለም ትኖራለህ፤ ዘመንህም የማይፈጸም ነው፤ ስም አጠራርህም ለልጅ ልጅ ነው።” 7 የመቃቢስ ልጆችም ይኸንና የሚመስለውን ሁሉ ዘመሩ፤ በእግዚአብሔር መታመንን መረጡ፤ ርኩስ መሥዋዕትን መብላትንም እንቢ አሉ፤ 8 ስለዚህም ሙታን እንደሚነሡ፥ ከትንሣኤም በኋላ ፍርድ እንደሚፈረድ ዐውቀው ስለ እግዚአብሔር ብለው ሰውነታቸውን ለሰማዕትነት ሰጡ። 9 የሙታንን ትንሣኤ የማታውቁና የማታምኑ ሰዎች! ከዚች ከምታልፍ ከምድራዊት ሕይወታቸው ይልቅ ኋለኛዪቱ ሕይወታቸው እንደምትበልጥ ዐውቀው ሰውነታቸውን በአንድነት ለሞት ከሰጡና ወንድማማችነታቸው ከአማረ ከእነዚህ ከአምስቱ ሰዎች የተነሣ ዕወቁ፤ 10 ሁሉ እንዲያልፍ ዐውቀው ስላመኑበት፥ ለጣዖትም ስላልሰገዱ፥ የሞተውንና የረከሰውንም መሥዋዕት ስላልበሉ፥ ከእግዚአብሔር ምስጋናን ያገኙ ዘንድ ሰውነታቸውን ለሞት ሰጡ። 11 ስለዚህም በኋለኛዪቱ ቀን በነፍስና በሥጋ ደስ እንደሚያሰኛቸው ዐውቀው ሚስትና ልጆች እያሏቸው የዚህን ዓለም ጣዕምና የሞትን ምሬት አላወቁም፤ በኋለኛዪቱም ቀን በነፍስና በሥጋ ትንሣኤ እንዲደረግ ዐውቀው ሰውነታቸውን ለሞት ሰጡ። 12 የእግዚአብሔርን ሥርዐት የጠበቁ ሕማምና ኀዘን፥ ሞትም በሌለበት በሚመጣው ዓለም ለልጅ ልጅና ለረጅም ዘመን፥ 13 የእግዚአብሔርን ቃል ከአመኑ ደጋግ ነገሥታትና መኳንንት ጋር እንደሚነግሡ ዐውቀው፥ ኋላም የሚደረገውን በልቡናቸው አይተው፥ በእሳት መካከል እንደ ሰም ሰውነታቸውን ለሞት ሰጡ። 14 ፊታቸውም ከፀሐይ ሰባት እጅ እንደሚያበራ፥ ሁሉም በነፍስና በሥጋ በሚነሣ ጊዜ በፍቅሩ ደስ እንደሚላቸው ተስፋ አድርገው ሰውነታቸውን ለሞት ሰጡ። |