ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 12 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በድንኳኑ ውስጥ ያዘዛችሁን ያልጠበቃችሁ፥ ከራሳችሁም ፈቃድ በቀር ፈቃዱን ያላደረጋችሁ የእስራኤል ኀያላን ወዮላችሁ! ይኸውም ትዕቢትና ትዝኅርት፥ ዝሙትና ስስት፥ ስካርና መጠጥ፥ በሐሰትም መማል ነው። 2 ስለዚህም ቍጣዬ በእሳት ፊት እንደ አለ ገለባ በእናንተ ላይ ይነድዳል፤ ተራራውንም እንደሚያቃጥል እሳት፥ የደቀቀውንም ትቢያ ከምድር አፍሶ ከሥራው የተነሣ ፍለጋው ወደማይገኝበት ወደ ሰማይ እንደሚበትነው፥ እንደ ዐውሎ ነፋስ፥ 3 እንዲሁ ክፋትን የሚሠሩአትን ሁሉ አጠፋቸዋለሁ ይላል የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር። ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔርንም አስቡት፤ የሚሳነውም የለም። 4 የሚወድዱትንም ይወድዳቸዋል፤ በትእዛዙም የሚሄዱትን በደላቸውንና ኀጢአታቸውን ያስተሰርይላቸዋል፤ በአለማመንም ደንቆሮዎችና የልብ ፈዛዞች አትሁኑ። 5 ልቡናችሁንም ለእግዚአብሔር የቀና አድርጉ፤ ነፍሳችሁን ታድኑ ዘንድ በእርሱ እመኑ፤ በመከራችሁም ቀን ከጠላታችሁ እጅ አድናችኋለሁ። 6 በምትጠሩኝም ጊዜ እነሆ ከእናንተ ጋር አለሁ እላችኋለሁ፤ ከጠላቶቻችሁም እጅ አድናችኋለሁ፤ በእኔም አምናችኋልና፥ ትእዛዜንም አድርጋችኋልና፥ ከሕጌም አልወጣችሁምና፥ እኔ የምወደውን ወዳችኋልና በመከራችሁ ቀን ቸል አልላችሁም ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር። 7 የሚወድዱትንም ይወድዳቸዋል፤ ርኅሩህና ይቅር ባይ ነውና፥ ትእዛዙን የሚጠብቁትን ይጠብቃቸዋል። 8 ቍጣውንም ብዙ ጊዜ ይመልስላቸዋል፤ ሥጋዊና ደማዊ እንደ ሆኑ የሚያውቃቸው ስለ ሆነ ይቅር ባይ ነውና፥ በመቅሠፍቱ ሁሉ አያጠፋም፤ ነፍሳቸውም ከሥጋቸው በተለየች ጊዜ ወደ መሬትነታቸው ይመለሳሉ። 9 ካለመኖር ፈጥሯቸዋልና፥ ካለመኖር ያመጣቸው ዘንድ እግዚአብሔር እስኪወድ ድረስ የሚኖሩበትን ቦታ አያውቁም፤ ዳግመኛም እርሱ ነፍሳቸውን ወሰደ፤ የመሬት ባሕርይንም ወደ መሬትነቱ መለሰ። 10 ዳግመኛም ፈቃዱ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣቸዋል። 11 እግዚአብሔርን የካደ ጺሩጻይዳን ግን በእግዚአብሔር ፊት መታበይን አበዛ፤ እስከ ወደደባትም ቀን ድረስ በተወው ጊዜ ራሱን ከፍ ከፍ አደረገ። 12 እንዲህም አለ፥ “ዘመኔ እንደ ሰማይ ዘመን ሆነ፤ ፀሐይንም የማወጣ እኔ ነኝ፤ እስከ ዘለዓለምም ድረስ አልሞትም።” 13 ይህንም ነገር ተናግሮ ሳይጨርስ ስሙ ጥልምያኮስ የሚባል መልአከ ሞት ወርዶ ልቡን መታው፤ በዚያችም ሰዓት ሞተ፤ ፈጣሪውን አላመሰገነውምና ከትዕቢቱ ብዛት፥ ከሥራውም ክፋት የተነሣ ከአማረ ኑሮው ተለይቶ ጠፋ። 14 የከለዳውያን ንጉሥ ሠራዊት ግን ሊወጉት ወድደው፥ ከከተማውና ከአገሩ አደባባይ ውጭ ሰፍረው ሳሉ በሞተ ጊዜ ወጥተው ሀገሩን አጠፉ፤ ከብቱንም ሁሉ ዘረፉ፤ ከቅጥር እስከሚጠጋ ወንድ ድረስ አላስቀሩም። 15 ገንዘቡን ሁሉ ዘረፉ፤ ቈሳቍሱንም ወሰዱ፤ ከተማውንም በእሳት አቃጥለው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። |