ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 11 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 የእግዚአብሔርን ሰው ሙሴን አስበው፤ በጸሎቱና በትሕትናው ይህን ያህል ሕዝቡን ሲጠብቅ አልተበሳጨም፥ አላጠፋምም፤ ነገር ግን ላሙትና እግዚአብሔርም በአንድ ጊዜ ያጠፋቸው ዘንድ ለወደደ ለወንድሙና ለእኅቱ በየዋህነቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ኀጢአታቸውን እንዲህ ሲል አስተሰረየላቸው፥ “አቤቱ ወገኖችህ በፊትህ በድለዋልና ወገኖችህን ይቅር በል፤ ቸልም አትበል፥ 2 በፊትህ በድያለሁና ኀጢአተኛ የምሆን እኔን ባርያህን ይቅር በለኝ፤ አንተ መሓሪ ነህና፥ ይቅር ባይም ነህና ለእነርሱም አስተስርይላቸው።” 3 እንደዚህም ሙሴ ለአሙት አስተሰረየላቸው። 4 ስለዚህም የዋህ ተባለ። 5 እግዚአብሔርም ከወንድሞቹ ከሌዋውያኑ ልጆች ሁሉ ይልቅ እጅግ ወደደው፤ ካህናቱንም ይሾማቸዋልና በእነርሱ ዘንድ እንደ እግዚአብሔር አስመሰለው። 6 የተደፋፈሩ የቆሬን ልጆች ግን በምድር በታች አሰጠማቸው፤ በሥጋና በነፍስ ሕያዋን ሳሉ ከከብቶቻቸውና ከድንኳኖቻቸው ጋራ ወደ ሲኦል አወረዳቸው፤ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ወድዶታልና ከትእዛዙም አልወጣምና የተናገረው ቃል ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይደረግለት ነበር። 7 አንተም እንዲሁ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባትተላለፍ እግዚአብሔር ፈቃድህን ያደርግልሃል፤ ነገርህንም ይወድልሃል፤ መንግሥትህንም ይጠብቅልሃል። 8 ከሙሴ ትእዛዝ የወጡ የቆሬና የአሳፍ ልጆችም ለእግዚአብሔር ልቡናችሁን አቅኑ ስላላቸው በእርሱ አንጐራጐሩ። 9 “እኛስ በምስክሩ ድንኳን የክህነት ሥራ የምንሠራ የሌዊ ልጆች አይደለንምን?” አሉት። 10 ያጥኑም ዘንድ ጥናቸውን ያዙ፤ ሄደውም አጠኑ፤ እግዚአብሔር ግን ጸሎታቸውን አልተቀበለም፤ በጥናቸው እሳትም ተቃጠሉ፤ በእሳት እንደሚቀልጥ ሰምም ቀለጡ፤ ከእነርሱም አንድ ሰው ስንኳ አልቀረም፤ “በሰውነታቸው መቃጠል ጥናቸው ከብሯል” ብሏልና በእግዚአብሔር ትእዛዝ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያ ከገቡት ከጥናቸው በቀር ልብሶቻቸውና አጥንቶቻቸው አልቀሩም። 11 ስለዚህም እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፥ “ጥናቸውን ወደ ድንኳን ሰብስቡ፤ ከውጭ ጀምሮ እስከ ውስጥ ድረስ ሁሉን ላዘጋጀሁለት ለቤቴ መሣሪያ ይሁን።” 12 የተቀደሰች የድንኳንዋንም መሣሪያ አዘጋጀ፤ መክደኛውንና ቀለበቱን፥ የኪሩቤልን ሥዕልና ባሕሩን አዘጋጀ። 13 ሰኑንና መጋረጃውን፥ ስክተቱንና የድንኳኑን ዙሪያ ዕድሞ፥ ጋኖችንና በምስክሩ ድንኳን የሚሠዉበት መሠዊያውን ሠራ። 14 የፈቃዱን መሥዋዕትና የሰላሙን መሥዋዕት፥ የስእለቱንና የኀጢአቱን መሥዋዕት፥ የማታውንና የጧቱንም መሥዋዕት ሠዉ። 15 ሥራ ይሠሩባት ዘንድ በምስክሩ ድንኳን ለሙሴ ያዘዘውን ሁሉ አዘዛቸው። 16 ማርና ወተትን የምታስገኝ፥ ለአብርሃም የማለለትን፥ ያባቶቻቸውን ርስት ይሰጣቸው ዘንድ ተስፋ በሰጣቸው በፈጣሪያቸው በእግዚአብሔር በሕጉ ድንኳን ውስጥ ስሙ በእነርሱ ይመሰገን ዘንድ ለአምላካቸው መገዛትን አላቃለሉም። 17 ለይስሐቅ ማለለት፤ ለያዕቆብም አምልኮቱን አጸናለት። 18 በምስክሩ ድንኳንም ለሙሴና ለአሮን አጸናላቸው፥ 19 በኢየሩሳሌም በድንኳኑና ሰሎሞን በሠራው ቤተ መቅደስ የእግዚአብሔር ማደሪያ፥ የልዑልም የስሙ ማረፊያ፥ የእስራኤልም ቅዱስ ማደሪያ እስኪሆን ድረስ ለሳሙኤልና ለኤልያስ አምልኮቱን አጸናላቸው። 20 በየዋህነት ለሚኖሩ ለካህናቱ የሚገለጥባት መለመኛና የኀጢአት ማስተስረያ ናትና። 21 ፈቃዱንም ለሚያደርጉ ሰዎች ልመናቸውን የሚሰማባት ቦታ ናት። 22 የእስራኤልም ቅዱስ የእግዚአብሔር ሕጉ የሚሠራባት ናትና። 23 ለእስራኤል ቅዱስ ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ ሊሆን መሥዋዕት የሚሠዋባት፥ ዕጣንም የሚታጠንባት ናትና። 24 በምስክሩ ድንኳን ውስጥም ይቅር በሚልበት በመክደኛው ላይ ሆኖ ይናገር ነበር፤ ለመረጣቸው ለያዕቆብ ልጆች፥ በእግዚአብሔር በሕጉና በትእዛዙ ጸንተው ለሚኖሩ ለቅዱሳኑም የእግዚአብሔር ብርሃኑ ይገለጥላቸው ነበር። 25 የሚገዳደሩ ግን ምድር እንዳሰጠመቻቸው እንደ ቆሬ ልጆች ይሆናሉ፤ እንዲሁም ኃጥኣን እስከ ዘለዓለም ድረስ መውጫ ወደሌላት ወደ ገሃነም እሳት ይገቡ ዘንድ አላቸው። |