ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 እናንተም ነገሥታቱና መኳንንቱ በሰይጣን ጎዳና አትሂዱ። ነገር ግን የፈጠራችሁን፥ እስከ ዛሬም ድረስ የጠበቃችሁን እግዚአብሔርን ፍሩት። 2 ሁሉንም በሚገዛ በእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ ጸንታችሁ ኑሩ። 3 የእስራኤል ልጆች የኬጤዎንንና የከናኔዎንን፥ የፌርዜዎንንም ሀገር ይወርሱ ዘንድ ወደ አማሌቅ በመጡ ጊዜ የሴፎር ልጅ ባላቅ፥ 4 በለዓምን፥ “አንተ የረገምኸው የተረገመ፥ የመረቅኸውም የተመረቀ ነውና ትረግምልኝ ዘንድ ና፤ እኔም የሚያከብርህን ብዙ ወርቅና ብር እሰጥሃለሁ” ብሎታልና። 5 በለዓምም የጥንቆላውን ዋጋ ተስፋ አድርጎ መጣ፤ የሴፎር ልጅ ባላቅም የእስራኤል ልጆች የሰፈሩበትን ቦታ አሳየው፤ 6 ሟርቱንም አደረገ፤ መሥዋዕቱንም ሠዋ፤ የሰቡትንም ላሞችንና በጎችን አረደ፤ የእስራኤልንም ልጆች ይረግማቸው ዘንድ ወደደ። 7 እግዚአብሔር ግን ይረግማቸው ዘንድ አልወደደም፤ ርግማንን ወደ ምርቃት በቃሉ መለሳት እንጂ። 8 እንዲህም አለ፥ “አንተ እግዚአብሔር የመረጠው ሕዝብ ነህና፥ ከሰማይ የሚመጣ የፍቁር ማደሪያም ነህና የሚመርቁህ የተመረቁ ይሁኑ፤ የሚረግሙህም የተረገሙ ይሁኑ” አለ። 9 ከዚህም በኋላ በፊቱ በመረቃቸው ጊዜ የሴፎር ልጅ ባላቅ አዘነ፤ ፈጽሞም ተቈጣ፤ ይረግማቸውም ዘንድ አዘዘ። 10 በለዓምም፥ “እግዚአብሔር የመረቀው ወገን ወደዚህ ሀገር መጥትዋልና እግዚአብሔር የመረቃቸውን እኔ አልረግምም” አለው። 11 የሴፎር ልጅ ባላቅም በለዓምን አለው፥ “እኔ ትረግምልኝ ዘንድ ወድጄ ነበር፤ አንተ ግን አልረገምኻቸውም፤ በፊቴም ፈጽመህ መረቅኻቸው፤ አንተም ብትረግምልኝና ስጠኝ ብትለኝ እኔ ቤት ሙሉ ወርቅና ብር በሰጠሁህ ነበር፤ አንተ ግን ፈጽመህ መረቅኻቸው፤ ለእኔም በጎ አላደረግህም፤ እኔም ለአንተ በጎ ነገር አላደርግም።” 12 በለዓምም፥ “እግዚአብሔር በአንደበቴ ያደረገውን ቃል እርሱን እናገራለሁ እንጂ እኔስ የእግዚአብሔርን ቃል ቸል ማለትና መተላለፍ አልችልም። 13 እኔስ ከነፍሴ ገንዘብን አልወድድም፤ ገንዘብን ብወድ የተመረቀ ወገንን እንዳልረግም እግዚአብሔር ይቈጣኛልና” አለ። 14 እግዚአብሔር አባታቸው ያዕቆብን፥ “የሚመርቁህ የተመረቁ ይሁኑ፤ የሚረግሙህም የተረገሙ ይሁኑ” ብሎታልና፤ 15 የሚመርቅህም ሁሉ የተመረቀ ነው፤ ያለ ፍርድም የሚረግምህ የተረገመ ነው፤ እግዚአብሔር አንተን ይወድህ ዘንድ ጎዳናህንና ሥራህን አከናውን። 16 እግዚአብሔርንም በክፋታቸው እንዳሳዘኑት፥ እርሱም ቸል እንዳላቸው እንደ ቀደሙ ሰዎች አትሁን፤ በጥፋት ውኃም ያጠፋቸው አሉ። 17 በጠላቶቻቸውም እጅ ያጠፋቸው አሉ፤ መከራ ያጸኑባቸው ክፉዎች ጠላቶችን አምጥቶ ነገሥቶቻቸውን ከካህናቶቻቸውና ከነቢያቶቻቸው ጋራ ማረኳቸው። 18 ወደማያውቁት ወደ ባዕድ ሀገርም አደረሷቸው፤ ፈጽመውም ማረኳቸው፤ ገረፉአቸውም፤ ሀገራቸውንም አጠፉ። 19 የቅድስቲቱን ከተማ አጥሯንና ቅጥሯን አፍርሰዋልና ኢየሩሳሌምን እንደ እርሻ አደረጓት። 20 ካህናቱም ተማረኩ፤ ሕጉም ፈረሰ፤ አርበኞችም በጦር ወደቁ። 21 ባልቴቶችም ተማረኩ፤ ለሞቱ ባሎቻቸውም አላለቀሱም፤ ተማርከዋልና ለራሳቸው አለቀሱ፤ 22 ሕፃናትም አለቀሱ፤ ሽማግሎችም አፈሩ፤ የሽማግሌውንና የሽበታሙን ፊት አልራሩም። 23 ለቆንጆዎችና በሕግ ላሉም አልራሩም፤ በአገራቸው ያገኙትንም ሁሉ አጠፉ፤ ቤተ መቅደስን አስቀድሞ ያፈርስ ዘንድ በወደደ ጊዜ እግዚአብሔር ወገኖቹን ተቈጥትዋልና ወደማያውቁት ወደ ባዕድ ሀገር ማርከው ወሰዷቸው። 24 ስለዚህም እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ቸል ባላቸው ጊዜ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንደ እርሻ እንድትታረስ አደረጋት፤ ሁልጊዜ ፈጣሪያቸውን ያሳዝኑታልና። 25 እርሱ ግን በምንም አንድ ጊዜ አላጠፋቸውም፤ ስለ አባቶቻቸው ይራራላቸዋልና የሚራራላቸው ስለ ራሳቸው አይደለም። በእውነት የነገሡ፥ በፈጣሪያቸውም ፊት በቀና ሕግ ጸንተው የኖሩ አባቶቻቸውን አብርሃምንና ይስሐቅን ያዕቆብንም ይወዳቸዋልና ነው እንጂ። 26 እርሱም እጥፍ በሆነ ክብር ላይ ሾማቸው፤ በሰማይና በምድር ያለ ሁለት መንግሥትንም አገኙ። 27 እንዲሁም በሚያልፍ በዚህ ዓለም የምትኖሩ እናንተ ነገሥታቱና መኳንንቱ በሚገባ ሥራ ጸንተው የኖሩ ከእናንተ አስቀድሞ የነበሩ አባቶቻችሁ መንግሥተ ሰማያትን እንደ ወረሱ፥ ስማቸው ለልጅ ልጅ ያማረ እንደ ሆነ አስቧቸው። 28 አንተም መንግሥትህን ያቀናልህ ዘንድ መልካም አኑዋኑዋራቸው እግዚአብሔርን እንዳገለገሉት ከአንተ አስቀድሞ እንደ ነበሩ እንደ ደጋጎች ነገሥታት ስምህን መልካም ያደርግልህ ዘንድ ሥራህን አቅና። |