ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ መቃብያን ካልእ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 መቃቢስ አይሁድን በሶርያ በሁለቱ ወንዞች መካከል አግኝቶ ከኢያቦቅ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም አደባባይ ድረስ በሸለቆዎቻቸው እንደ ገደላቸው፥ ቅድስቲቱንም ከተማ እንዳጠፋት የሚናገር መጽሐፍ ይህ ነው። 2 ከሰማርያ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም አደባባይ ድረስ፥ እስከ አውራጃዋም ሁሉ ድረስ ሰፍረዋልና ከጥቂቶች በቀር ሳያስቀሩ በጦር ገደሉ። ኤዶማውያንና ሶርያውያን፥ አማሌቃውያንም የኢየሩሳሌምን ከተማ ካጠፋው ከሞዓብ ሰው ከመቃቢስ ጋር አንድ ሆነዋልና። 3 የእስራኤልም ልጆች በበደሉ ጊዜ ሞዓባዊውን መቃቢስን አስነሣባቸው፤ እርሱም ሁሉን በሰይፍ ገደላቸው። 4 ስለዚህም ነገር የእግዚአብሔር ጠላቶች በቅድስት ከተማው ላይ ደነፉ፤ በወንጀላቸውም ተማማሉ። 5 ኤዶማውያንና ኢሎፍላውያንም ሰፈሩ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ተገዳደሩ እርሱ ልኳቸዋልና የእግዚአብሔርን ከተማ ይበቀሉ ጀመር። 6 የዚያም የመቃቢስ ሀገሩ የሞዓብ ሬማት ናት፤ ከሀገሩም በኀይል ተነሥቶ አብረውት ከአሉ ሰዎች ጋራ ተማማለ። 7 የእግዚአብሔርንም ከተማ ያጠፉ ዘንድ በመስጴጦምያ-ጌላቡሄ ሸለቆዎች እስከ ሶርያ ድረስ ሰፈሩ፤ በዚያም ኢሎፍላውያንንና አማሌቃውያንን ለመነ፤ በወንጀልም ከእርሱ ጋራ አንድ ይሆኑ ዘንድ ብዙ ወርቅንና ብርን፥ ፈረሶችንና ሠረገላዎችን ሰጣቸው። 8 በአንድነትም መጥተው አንባዪቱን ናዷት፤ በውስጧ የሚኖሩ ሰዎች ደምንም እንደ ውኃ አፈሰሱ። 9 ኢየሩሳሌምንም እንደ ተክል ጠባቂ ጎጆ አደረጓት፤ በውስጧም ድምፅ አሰማባት፤ እግዚአብሔርም የማይወድደውን የክፋት ሥራ ሁሉ አደረገ፤ ጽድቅንና ቅድስናን የተመላች የእግዚአብሔርንም ከተማ አረከሱ። 10 “የባሮችህን እሬሳ ለሰማይ ወፎች ምግብ አደረጉ። የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድረ በዳ አራዊት መብል አደረጉ።” 11 ባልቴቲቱንና የሙት ልጁን ቀሙ፤ ሰይጣን እንዳስተማራቸው እግዚአብሔርን ሳይፈሩ አድርገዋልና ኵላሊትንና ልቡናን የሚመረምር እግዚአብሔር እስኪቈጣ ድረስ በፀነሱ ሴቶች ሆድ ያለውን ፅንስ አወጡ። 12 በእግዚአብሔር ሕዝብም ላይ ክፉን ስለ አደረጉ ደስ እያላቸው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፤ ከቅድስት ከተማ የማረኩትንም ምርኮ ወሰዱ። 13 ተመልሰውም ወደ ቤታቸው በገቡ ጊዜ ደስታን፥ ዘፈንንና ጭብጨባን አደረጉ። |