2 ነገሥት 5 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ንዕማን ከለምጽ እንደ ነጻ 1 የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት አለቃ ንዕማንም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ለሶርያ ደኅንነትን ስለ ሰጠ፥ በጌታው ዘንድ ታላቅና ክቡር ሰው ነበረ፤ ሰውዬውም ጽኑዕ፥ ኀያል ነበረ፤ ነገር ግን ለምጻም ነበረ። 2 ከሶርያውያንም ጋር ወደ ሰልፍ በወጣ ጊዜ ከእስራኤል ምድር ታናሽ ብላቴና ሴት ማረከ፤ ለሚስቱም አገልጋይ አደረጋት። 3 እመቤቷንም፥ “ጌታዬ በሰማርያ ወደሚኖረው ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ነቢዩ ይሄድ ዘንድ በተገባው ነበር፤ ከለምጹም በፈወሰው ነበር” አለቻት። 4 ሚስቱም ወደ እርሱ ገብታ፥ “ከእስራኤል ሀገር የመጣች ይች ብላቴና እንደዚህና እንደዚህ አለች” ብላ ነገረችው። 5 የሶርያም ንጉሥ ንዕማንን፥ “ሂድ፥ ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እልካለሁ” አለው። እርሱም ሄደ፤ ዐሥርም መክሊት ብር፥ ስድስት ሺህም ወቄት ወርቅ፥ ዐሥርም መለወጫ ልብስ በእጁ ወሰደ። 6 ወደ እስራኤልም ንጉሥ፦ ደብዳቤውን አደረሰ። ደብዳቤውም እንዲህ ይላል፥ “ደብዳቤው ካንተ ዘንድ በደረሰ ጊዜ ባለሟሌን ንዕማንን ወደ አንተ ልኬዋለሁና ከለምጹ ፈውሰው።” 7 የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ባነበበ ጊዜ ልብሱን ቀድዶ፥ “ሰውን ከለምጹ እፈውስ ዘንድ ይህ ሰው ወደ እኔ መስደዱ እኔ በውኑ ለመግደልና ለማዳን የምችል አምላክ ነኝን? ተመልከቱ፥ የጠብ ምክንያት እንደሚፈልግብኝ ተመልከቱ” አለ። 8 ኤልሳዕም የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን እንደ ቀደደ በሰማ ጊዜ፥ “ልብስህን ለምን ቀደድህ? ንዕማን ወደ እኔ ይምጣ፤ በእስራኤልም ዘንድ ነቢይ እንዳለ ያውቃል” ብሎ ወደ ንጉሡ ላከ። 9 ንዕማንም በፈረሱና በሰረገላው መጣ፤ በኤልሳዕም ቤት ደጃፍ ውጭ ቆመ። 10 ኤልሳዕም፥ “ሂድ፥ በዮርዳኖስም ሰባት ጊዜ ተጠመቅ፤ ሰውነትህም ይፈወሳል፤ አንተም ንጹሕ ትሆናለህ” ብሎ ወደ እርሱ መልእክተኛ ላከ። 11 ንዕማን ግን ተቈጥቶ ሄደ፤ እንዲህም አለ፥ “እነሆ፥ ወደ እኔ የሚመጣ፥ ቆሞም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፥ የለምጹንም ስፍራ በእጁ ዳስሶ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር። 12 የደማስቆ ወንዞች ባብናና ፋርፋ ከእስራኤል ውኆች ሁሉ አይሻሉምን? ሄጄስ በእነርሱ ውስጥ መጠመቅና መንጻት አይቻለኝም ኖሮአልን?” ብሎ በቍጣ ተመልሶ ሄደ። 13 አገልጋዮቹም ወደ እርሱ መጥተው፥ “ነቢዩ ታላቅ ነገር ቢነግርህ ባደረግኸው ነበር፤ ይልቁንስ፦ ተጠመቅና ንጹሕ ሁን ቢልህ እንዴት ነዋ!” ብለው ተናገሩት። 14 ንዕማንም ወረደ፤ የእግዚአብሔርም ሰው ኤልሳዕ እንደ ተናገረው በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ተጠመቀ፤ ሰውነቱም እንደ ገና እንደ ትንሽ ብላቴና ሰውነት ሆኖ ተመለሰ፤ ንጹሕም ሆነ። 15 እርሱም ከጭፍራው ሁሉ ጋር ወደ ኤልሳዕ ተመለሰ፤ ወደ እርሱም ደርሶ በፊቱ ቆመና፥ “እነሆ፥ በእስራኤል ነው እንጂ በምድር ሁሉ አምላክ እንደሌለ ዐወቅሁ፤ አሁንም ከአገልጋይህ በረከት ተቀበል” አለው። 16 ኤልሳዕም፥ “በፊቱ የቆምሁት ሕያው እግዚአብሔርን! አልቀበልም” አለ። ይቀበለውም ዘንድ ግድ አለው፤ እርሱ ግን እንቢ አለ። 17 ንዕማንም፥ “እኔ አገልጋይህ ከእንግዲህ ወዲህ ከእግዚአብሔር በቀር ለሌሎች አማልክት የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ሌላ መሥዋዕት አላቀርብምና ሁለት የበቅሎ ጭነት አፈር ለአገልጋይህ ይስጡት። 18 እግዚአብሔርም የእኔን የአገልጋይህን ኀጢአት በዚህ ነገር ብቻ ይቅር ይበለኝ፤ ጌታዬ በዚያ ይሰግድ ዘንድ እጄን ተደግፎ ወደ ሬማን ቤት በገባና በሰገደ ጊዜ፥ እኔም በሬማን ቤት በሰገድሁ ጊዜ፥ እግዚአብሔር በዚህ ነገር እኔን አገልጋይህን ይቅር ይለኛል” አለ። 19 ኤልሳዕም ንዕማንን፥ “በሰላም ሂድ” አለው። ጥቂት መንገድም ከእርሱ ራቀ። ግያዝ ከንዕማን ገንዘብና ልብስ እንደ ተቀበለና በኤልሳዕ እንደ ተረገመ 20 የኤልሳዕም ሎሌ ግያዝ፥ “ጌታዬ ሶርያዊውን ይህን ንዕማንን ማረው፤ ካመጣለትም ነገር ምንም አልተቀበለም፤ ሕያው እግዚአብሔርን! በስተኋላው እሮጣለሁ፤ ከእርሱም አንዳች እወስዳለሁ” አለ። 21 ግያዝም ንዕማንን ተከተለው፤ ንዕማንም ዘወር ብሎ ወደ እርሱ ሲሮጥ ባየው ጊዜ ሊገናኘው ከሰረገላው ወርዶ፥ “ሁሉ ደኅና ነውን?” አለው። 22 እርሱም፥ “ሁሉ ደኅና ነው፦ አሁን ከነቢያት ወገን የሆኑ ሁለት ጐልማሶች ከተራራማው ከኤፍሬም ሀገር ወደ እኔ መጥተዋልና፤ አንድ መክሊት ብርና ሁለት መለወጫ ልብስ ትሰጣቸው ዘንድ እለምንሃለሁ ብሎ ጌታዬ ላከኝ” አለው። 23 ንዕማንም፥ “ሁለት የብር መክሊት ውሰድ” አለው፤ ሁለቱንም መክሊት ብር ተቀብሎ በሁለት ከረጢት ውስጥ ጨመረና ከሁለት መለወጫ ልብስ ጋር ለሁለት ሎሌዎቹ አስያዘ፤ እነርሱም ተሸክመው በፊቱ ሄዱ። 24 ወደ ስውር ቦታም በደረሱ ጊዜ ከእጃቸው ወስዶ በቤቱ ውስጥ አኖራቸው፤ ሰዎቹንም አሰናበተ። 25 ከዚህም በኋላ ገብቶ፥ በጌታው ፊት ቆመ፤ ኤልሳዕም፥ “ግያዝ ሆይ፥ ከወዴት መጣህ?” አለው። እርሱም፥ “እኔ አገልጋይህ ወዴትም አልሄድሁም” አለ። 26 እርሱም፥ “ያ ሰው ከሰረገላው ወርዶ ሊቀበልህ በተመለሰ ጊዜ ልቤ ከአንተ ጋር አልሄደምን? አሁንም ወርቁንና ልብሱን፥ ተቀብለሃል፤ ለወይን ቦታ፥ ለመሰማርያ ቦታና ለዘይት ቦታ፥ ለላሞችና ለበጎች፥ ለወንዶችና ለሴቶች ባሮች ይሁንህ። 27 ነገር ግን የንዕማን ለምጽ በአንተና በዘርህ ላይ፥ ለዘለዓለም ይመለስ” አለው። እንደ በረዶም ለምጻም ሆኖ ከእርሱ ዘንድ ወጣ። |