ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 4 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ንጉሥ አሸናፊነት የቀረበ ሐተታ 1 ንጉሥ ያሸንፋል ያለው ሁለተኛውም ይናገር ጀመረ። 2 “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ሰዎች ምድርን የሚያሸንፏት፥ ባሕርንም፥ በውስጧ ያለውንም ሁሉ የሚገዙ አይደለምን? 3 ንጉሥም ለእነርሱ ጌታቸው ነው፤ ፈጽሞም ይገዛቸዋል፤ እርሱ ያዘዛቸውንም ሁሉ ያደርጋሉ። 4 ባልንጀራችሁን ግደሉ ቢላቸውም ይገድላሉ ወደ ጦርነትም ሂዱ ቢላቸው ይሄዳሉ፤ ተራሮችንም ይንዳሉ፤ አጥሩንና ግንቡንም ያፈርሳሉ። 5 የንጉሡንም ትእዛዝ እንቢ እንዳይሉ ይገድላሉ፤ ይገደላሉም፤ ድል ቢያደርጉም የማረኩትን ምርኮ ሁሉ ለንጉሡ ያገባሉ። 6 “ያልዘመቱና ያልተዋጉ፥ ምድርን የሚያርሱ እነርሱ ዘርተው አዝመራቸውን ባገቡ ጊዜ ግብሩን ለንጉሡ ይሰጣሉ። ለንጉሡም ግብር እንዲከፍል አንዱ ሌላውን ያስገድደዋል። 7 እርሱ ግን አንድ ብቻ ነው፤ ግደሉ ቢላቸው ይገድላሉ፤ ተዉ ቢላቸውም ይተዋሉ። 8 ግረፉ ቢላቸውም ይገርፋሉ፤ ገንቡ ቢላቸውም ይገነባሉ፤ አፍርሱ ቢላቸውም ያፈርሳሉ። 9 ቍረጡ ቢላቸው ይቈርጣሉ፤ ትከሉ ቢላቸውም ይተክላሉ። 10 ሕዝቡ ሁሉና ሠራዊቱም ላንድ ለእርሱ ይታዘዙለታል፤ ከዚህም ሁሉ ጋራ እርሱ ተቀምጦ በልቶና ጠጥቶ ይተኛል። 11 ሌላውም ዙሪያውን ይጠብቃል፤ ከእነርሱም ተለይቶ ሄዶ ጉዳዩን ማድረግ የሚችል አንድም የለም፤ በማናቸውም ነገር እንቢ ይሉት ዘንድ አይችሉም። 12 እናንተ ሰዎች ሆይ፥ ሁሉ እንዲህ የሚታዘዝለት ንጉሥ አያሸንፍምን?” ከዚህም በኋላ ዝም አለ። ስለ ሴት አሸናፊነት የቀረበ ሐተታ 13 ስለ ሴቶችና ስለ እውነት የተናገረው ሦስተኛውም ይናገር ጀመረ፤ እርሱም ዘሩባቤል ነው። እርሱም እንዲህ አለ፦ 14 “እናንተ ሰዎችሆይ፥ ንጉሡ ታላቅ አይደለምን? ሰዎቹስ ብዙ አይደሉምን? ወይንስ ብርቱ አይደለምን? እኒህንስ የሚገዛቸውና የሚያዝዛቸው ማነው? ሴቶች አይደሉምን? 15 ሴቶች ምድርንና ባሕርን የሚገዙ ንጉሡንና ሕዝቡን ሁሉ ወልደዋል። 16 ከእነርሱም ተወለዱ፤ እነርሱም ከእርሱ ወይን የሚገኝበት የወይን ተክልን የሚተክሉ ሰዎችን አሳደጉ። 17 እነርሱም ለሰዎች ልብስን ይሠራሉ፤ ለወንዶችም ክብርን ያደርጋሉ፤ ወንዶችም ያለ ሴት መኖር አይቻላቸውም። 18 ሰዎች ምንም እንኳ ብሩንና ወርቁን፥ መልካሙንም ዕቃ ሁሉ ቢሰበስቡ፥ መልኳ ያማረና ደም ግባትዋ የተወደደ አንዲት ሴትን ባዩ ጊዜ፥ 19 ያን ሁሉ ረስተው እርሷን ይመለከታሉ፤ አፏንም ያያሉ፤ ሁሉም ያደንቋታል፤ ከወርቅና ከብር፥ ካማረውም ዕቃ ሁሉ እርሷን ይመርጧታል። 20 ሰውም ያሳደገውን አባቱንና ሀገሩን ትቶ ሚስቱን ይከተላል። 21 ስለ ሚስቱም ነፍሱን ይሰጣል፤ አባትና እናቱን፥ ሀገሩንም አያስባቸውም። 22 በዚህም ሴቶች እንደሚያሸንፏችሁ ታውቃላችሁ፤ ጥራችሁና ደክማችሁም ሁሉን አምጥታችሁ ለሴቶች የምትሰጧቸው አይደላችሁምን? 23 ወንድ ጦሩን ይዞ ወጥቶ ይሄዳል፤ ይሰርቃል፤ ይዘርፋልም፤ በባሕሩና በወንዙ ይጓዛል፤ 24 አንበሳንም እያየ ይሄዳል፤ በጨለማም ይሄዳል። በሰረቀና በነጠቀ፥ በዘረፈም ጊዜ ሁሉን ለሚወዳት ይሰጣል። 25 ወንድ ከወለዱት ከእናቱና ከአባቱ ይልቅ ሚስቱን ይወዳታል። 26 በሴቶች ምክንያት ልባቸው የጠፋ፥ ስለ እነርሱም የተገዙና ባሮች የሆኑ ብዙዎች ናቸው። 27 በሴቶችም ምክንያት የሞቱ፥ የተሳሳቱና የበደሉ ብዙዎች ናቸው። 28 “አሁንም አታምኑኝምን? ንጉሥ በሥልጣኑ ታላቅ አይደለምን? ሕዝቡስ ሁሉ ባዩት ጊዜ እርሱን መንካት የሚፈሩ አይደለምን? 29 እነሆ የንጉሡ ዕቅብት የክቡር የበርጠቁ ልጅ ኤጴሜን በንጉሡ ቀኝ ትቀመጣለች። 30 የንጉሡን ዘውድ ከራሱ ላይ አውርዳ በራሷ ላይ ትደፋለች፤ ንጉሡንም በግራ እጇ በጥፊ ትመታዋለች። 31 ከዚህም ሁሉ ጋራ ንጉሥ አፏን ያያል፤ ብትስቅ ይስቃል፤ ብትቈጣም ትናገር ዘንድ፥ ቍጣዋም ይበርድ ዘንድ ያቈላምጣታል። 32 እናንተ ሰዎች፥ እንዲህ የሚያደርጉ ሴቶች አያሸንፉምን?” ስለ እውነት አሸናፊነት የቀረበ ሐተታ 33 ከዚህም በኋላ ንጉሡና መኳንንቱ እርስ በርሳቸው ተያዩ፤ ከዚህም በኋላ የእውነትን ነገር ይናገር ጀመረ። 34 እንዲህም አለ፥ “እናንተ ሰዎች ሆይ፥ እውነት የሚያሸንፍ አይደለምን? ምድርስ ታላቅ ነው፤ ሰማይም ከፍ ያለ ነው፤ ፀሐይም በዙረቱ ፈጣን ነው፤ ባንዲት ቀን ሰማይን ዙሮ በቀኙ ወደ ቦታው ይመለሳልና 35 እንዲህ የሚያደርግ ታላቅ አይደለምን? እውነትም ታሸንፋለች፤ ከዚህም ሁሉ ትበልጣለች። 36 ዓለም ሁሉ እውነትን ይጠራታል፤ ሰማይም ይባርካታል፤ ፍጥረትም ሁሉ ለእርሷ ይንቀጠቀጣል፤ ይናወጣልም፤ ከእውነትም ጋር ዐመፃ አይገኝም። 37 ወይን በደለኛ ነው፤ ንጉሥም በደለኛ ነው፤ ሴቶችም በደለኞች ናቸው፤ የሰው ልጅም በደለኛ ነው፤ ሥራቸውም ሁሉ በደል ነው፤ ይህ ሁሉ በእውነት ዘንድ የለም፤ እነዚህም ሁሉ በበደላቸው ይሞታሉ። 38 “እውነት ግን ሁልጊዜ ታሸንፋለች፤ ሕይወትም ናት፤ ለዘለዓለሙም ፈጽማ ጸንታ ትኖራለች። 39 በእርሷ ዘንድ ልዩነትና ለፊት ማዳላት የሉም፤ ነገር ግን እውነት በሐሰትና በክፉ ሁሉ አትኖርም። ሰዎች ሁሉም ሥራዋን ይወድዳሉ። 40 በፍርድዋም ዐመፅ የለባትም፤ እርስዋም ታሸንፋለች፥ መንግሥት፥ ገናናነትና በዓለም ውስጥ ያለ ሥልጣን ሁሉ የእርስዋ ነው፤ መንግሥት የእርሱ የሆነ እግዚአብሔር ይመስገን” ብሎ ዝም አለ። የዘሩባቤል ሽልማት 41 ከዚህም በኋላ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ፥ “እውነት ታላቅ ናት! ፈጽማም ታሸንፋለች!” አሉ። 42 ንጉሡም፥ “የምትወድደውን ከተጻፈው ሁሉ አብልጠህ ለምን፤ እኔም እሰጥሃለሁ። አንተ ዐዋቂ ሆነሃልና፥ ተለይተህም ከእኔ ጋር ትቀመጣለህ፤ የእኔም ዘመድ ትሆናለህ” አለው። 43 እርሱም ንጉሡን እንዲህ አለው፥ “በነገሥህ ጊዜ ኢየሩሳሌምን ትሠራት ዘንድ የተሳልኸውን ስእለት ዐስብ። 44 ከኢየሩሳሌም የተወሰዱትን፥ ቂሮስ ባቢሎንን ለማጥፋት በጀመረ ጊዜ ለይቶ ያኖራቸውንና ወደዚያ ለመመለስ የተሳላቸውን ዕቃዎችን ትመልስ ዘንድ ዐስብ። 45 አንተም ከለዳውያን ይሁዳን ባጠፏት ጊዜ ኤዶማውያን ያቀጠሏትን ቤተ መቅደስ ትሠራ ዘንድ ተስለሃል። 46 አሁንም ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ የምማልድህና የምለምንህ ይህ ነው፤ ካንተም የምፈልጋት ታላቅ ነገር ይህች ናት፥ ጌታዬ ለሰማይ አምላክ የተሳልኸውን ስእለትህን ታደርግ ዘንድ እሺ በለኝ፥ ካንደበትህ የወጣውንም አድርግ።” 47 ከዚህ በኋላም ንጉሡ ዳርዮስ አቅፎ ሳመው፤ እርሱንና ይሠሯት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም የሚወጡትን ከእርሱ ጋር ያሉትን ሁሉ ይሹ ዘንድ ወደ ግምጃ ቤት አዛዦችና ወደ አለቆች፥ ወደ መሳፍንቱና ወደ መኳንንቱ ሁሉ ደብዳቤዎችን ጻፈለት። 48 ከእርሱም ጋር ከተማዋን ይሠሩ ዘንድ የዋንዛውን እንጨት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያመጡ በቄሌ-ሶርያና በሊባኖስ ላሉ መሳፍንት ሁሉ ደብዳቤዎችን ጻፈ። 49 ኀይላቸው የሚሆኑ ባልንጀሮችንም ሁሉ ከመገዛታቸው ነጻ ያወጧቸው ዘንድ ከግዛቱ ወደ ይሁዳ ለሚወጡትም አይሁድ ሁሉ ጻፈ። የግምጃ ቤት አዛዦች፥ መሳፍንቱና መኳንንቱም ወደ በራቸው እንዳይገቡ ጻፈ። 50 ባውራጃቸው ላሉትም ግብሩን ይተዉላቸው ዘንድ፥ ኤዶማውያንም አጽንተው የያዙትን ቦታቸውን ለአይሁድ ይተዉ ዘንድ ጻፈ። 51 ሕንጻውም እስኪፈጸም ድረስ ለቤተ መቅደሱ ሥራ የሚሆን በየዓመቱ ሃያ መክሊት ወርቅ ይሰጧቸው ዘንድ ጻፈ። 52 እንደ ልማዳቸውም በሕጉ ሁልጊዜ በመሠዊያው ላይ ለሚሠዉት የዘወትር መሥዋዕት ዐሥራ ሰባት፥ በየዓመቱም ሌላ ዐሥር መክሊት ወርቅ ይሰጧቸው ዘንድ ጻፈ። 53 ከተማዋንም ለመሥራት ከባቢሎን ለሚመጡት ሁሉ ለእነርሱና ለልጆቻቸው አገዛዝን ይተውላቸው ዘንድ ጻፈ። 54 ለሚወጡ ካህናትም ሁሉ ምግባቸውንና የሚያገለግሉበት የአገልግሎት ልብሳቸውን ጻፈላቸው። 55 ለሌዋውያንም፦ የኢየሩሳሌምና የቤተ መቅደስ ሥራ እስኪፈጸም ድረስ ምግባቸውን ይሰጧቸው ዘንድ ጻፈላቸው። 56 ለሚያገለግሉና ከተማዋን ለሚሠሩ ሁሉ ምግባቸውን ይሰጧቸው ዘንድ ጻፈላቸው። 57 ቂሮስ ከባቢሎን ያወጣውን ንዋየ ቅድሳቱንም ሁሉ፥ ሁሉንም ቂሮስ እንዳዘዘላቸው ያደርጉ ዘንድ፥ እርሱም እንዲሁ እንዲያደርጉና ወደ ኢየሩሳሌም እንዲልኩ አዘዛቸው። የዘሩባቤል ጸሎት 58 ከዚህም በኋላ ወጣቱ በወጣ ጊዜ በኢየሩሳሌም አንጻር ፊቱን ወደ ሰማይ አቀና፤ የሰማይንም ንጉሥ አመሰገነው። 59 እንዲህም አለ፥ “ድል መንሣት ከአንተ ዘንድ ነው፤ ጥበብም ከአንተ ዘንድ ነው፤ ክብርም ለአንተ ነው፤ እኔም ያንተ ባሪያ ነኝ። 60 ጥበብን የሰጠኸኝ አንተም ቡሩክ ነህ፤ የአባቶቻችን ጌታ አመሰግንሃለሁ።” 61 ደብዳቤዎችንም ተቀብሎ ወደ ባቢሎን ሄደ፤ ይህንም ለወንድሞቹ ሁሉ ነገራቸው። 62 ያባቶቻቸውንም አምላክ አመሰገኑ፤ ዕረፍትን ሰጥትዋቸዋልና፥ ይቅርም ብሏቸዋልና፥ 63 ኢየሩሳሌምንና ስሙ የተጠራባት ቤተ መቅደስንም ይሠሩአት ዘንድ፤ ለመውጣት ፈቅዶላቸዋልና። በመሰንቆና በበገናም ደስ እያላቸው ሰባት ቀን ተቀመጡ። |