2 ዜና መዋዕል 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ሰሎሞን ለሕዝቡ ያሰማው ንግግር ( 1ነገ. 8፥12-21 ) 1 ያንጊዜም ሰሎሞን፥ “እግዚአብሔር፦ በጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብሎአል። 2 እኔም ለዘለዓለም የሚኖርበት ዝግጁና ቅዱስ ቤት ለስሙ ሠራሁ” አለ። 3 ንጉሡ ሰሎሞንም ፊቱን መልሶ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር። 4 እርሱም አለ፥ “ለአባቴ ለዳዊት በአፉ የተናገረ፥ በእጁም የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። 5 እርሱ፦ ሕዝቤን ከግብፅ ምድር ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ከእስራኤል ነገድ በዚያ ለስሜ ቤት ይሠራበት ዘንድ ከተማን አልመረጥሁም። በሕዝቤ እስራኤል ላይም ይነግሥ ዘንድ ሰውን አልመረጥሁም። 6 ነገር ግን ስሜ በዚያ እንዲጠራባት ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ። በሕዝቤም በእስራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ ብሎአል። 7 አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አስቦ ነበር። 8 እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን፦ ለስሜ ቤት ትሠራ ዘንድ በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም አደረግህ። 9 ነገር ግን ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራል እንጂ አንተ አትሠራልኝም አለው። 10 እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተተካሁ፤ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፤ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ። 11 ከሕዝቡም ከእስራኤል ጋር ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያለባትን ታቦት በዚያው ውስጥ አኖርሁ።” ሰሎሞን ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት ( 1ነገ. 8፥22-53 ) 12 ሰሎሞንም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ፊት በእግዚአብሔር መሠዊያ አንጻር ቆሞ እጆቹን ዘረጋ። 13 ሰሎሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ የሆነ የናስ መድረክ ሠርቶ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ መካከል ተክሎት ነበር፤ በላዩም ቆመ፤ በእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ፊት በጕልበቱ ተንበርክኮ እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ 14 እንዲህም አለ፥ “አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ በሰማይም በምድርም አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምታጸናና የምትጠብቅ አንተ ነህ። 15 ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት እንዲህ ብለህ የተናገርኸውን የጠበቅህ፥ በአፍህ ተናገርህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው በእጆችህ ፈጸምኸው። 16 አሁንም አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ በሕጌ ይሄዱ ዘንድ መንገዳቸውን ቢጠብቁ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አይታጣም ብለህ የተናገርኸውን ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት ጠብቅ፤ አጽናም። 17 አሁንም፥ አቤቱ፥ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ ለባሪያህ ለዳዊት የተናገርኸው ቃል ይጽና። 18 “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ሰማየ ሰማያትም ይወስንህ ዘንድ አይችልም፤ እንግዲያስ እኔ የሠራሁት ይህ ቤት ምንድን ነው? 19 ነገር ግን አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ ወደ ባሪያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ባሪያህ በዚች ዕለት በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ልመናውን ስማ። 20 ባሪያህ በዚህ ቤት የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ፦ በዚያ ስሜ ይሆናል ወዳልኸው ስፍራ፥ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ቀንና ሌሊት የተገለጡ ይሁኑ። 21 ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል በዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በተዘጋጀው በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል። 22 “ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ ይምልም ዘንድ በላዩ መሐላ ቢጭንበት፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢናዘዝ፥ 23 በሰማይ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህም ላይ ዳኛ ሁን፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፤ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑንም አጽድቀው፤ እንደ ጽድቁም ክፈለው። 24 “ሕዝብህ እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላት ፊት ድል ተመትተው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት በፊትህ ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ 25 አንተ በሰማይ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱም፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው። 26 “አንተን ስለ በደሉ ሰማያት በተዘጉ ጊዜ፥ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ በዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባዋረድሃቸውም ጊዜ ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፥ 27 አንተ በሰማይ ስማ፤ የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፥ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ አሳያቸው፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብን ስጥ። 28 “በምድር ላይ ራብ፥ ወይም ቸነፈር፥ ወይም ዋግ፥ ወይም አረማሞ፥ ወይም አንበጣ፥ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ ጠላቶቻቸውም የሀገሩን ከተሞች ከብበው ቢያስጨንቁአቸው፥ ማናቸውም መቅሠፍትና ደዌ ቢሆን፥ 29 ማንም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል ሁሉ፥ ማናቸውም ሰው ሕማሙንና ኀዘኑን ዐውቆ ጸሎትና ልመና ቢያደርግ፥ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥ 30 አንተ በተዘጋጀው በማደሪያህ በሰማይ ስማው፤ ይቅርም በለው፤ ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለው፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ልብ ታውቃለህና። 31 ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ በመንገዶችህም ይሄዱ ዘንድ። 32 “ከሕዝብህ ከእስራኤል ያልሆነ እንግዳ ስለ ታላቁ ስምህ፥ ስለ ብርቱውም እጅህ፥ ስለ ተዘረጋውም ክንድህ፥ ከሩቅ ሀገር መጥቶ በዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥ 33 አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ፥ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፥ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደ ተጠራ ያውቁ ዘንድ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ። 34 “ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ወደዚህች ከተማ፥ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለአንተ ቢጸልዩ፥ 35 ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፤ ፍርድንም ፍረድላቸው። 36 “የማይበድል ሰው የለምና አንተን ቢበድሉ፥ ብትቈጣቸውም፥ ለጠላቶቻቸውም አሳልፈህ ብትሰጣቸው፥ ሩቅም ወይም ቅርብ ወደ ሆነ ሀገር ጠላቶቻቸው ቢማርኩአቸው፥ 37 በተማረኩባትም ሀገር ሆነው በልባቸው ንስሓ ቢገቡ፥ በምርኮአቸውም ሀገር ሳሉ ተመልሰው፦ ኀጢአት ሠርተናል፥ በድለንማል፥ ክፉም አድርገናል ብለው ቢለምኑህ፤ 38 በተማረኩበትም ሀገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው፥ ወደ መረጥሃትም ከተማ፥ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ 39 ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በተዘጋጀ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ፍርድንም አድርግላቸው፤ አንተንም የበደሉህን ሕዝብህን ይቅር በል። 40 “አሁንም አምላኬ ሆይ፥ በዚህ ስፍራ ወደሚሆነው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ፥ ጆሮዎችህም የሚያደምጡ ይሁኑ። 41 አሁንም አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ከኀይልህ ታቦት ጋር ወደ ዕረፍትህ ተነሣ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ካህናትህ ደኅንነትን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም በደስታ ደስ ይበላቸው። 42 አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ከቀባኸው ሰው ፊትህን አትመልስ፤ ለባሪያህም ለዳዊት ምሕረትን አስብ።” |