1 ሳሙኤል 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የሳሙኤል እናት የሐና ጸሎት 1 ሐናም ጸለየች፤ እንዲህም አለች፦ “ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፤ ቀንዴም በአምላኬ በመድኀኒቴ ከፍ ከፍ አለ፤ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፤ በማዳንህም ደስ ብሎኛል። 2 እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የለምና፥ እንደ አምላካችንም ጻድቅ የለምና፤ አቤቱ፥ ከአንተም በቀር ቅዱስ የለም። 3 አትመኩ፤ የኵራት ነገሮችንም አትናገሩ፤ ፅኑዕ ነገርም ከአፋችሁ አይውጣ፤ እግዚአብሔር አምላክ ዐዋቂ ነውና፥ እግዚአብሔርም ዙፋኑን ያዘጋጃል። 4 የኀያላንን ቀስት ሰብሮአል፤ ደካሞችንም ኀይልን አስታጥቋቸዋል። 5 እንጀራ ጠግበው የነበሩ ተራቡ፤ ተርበውም የነበሩ ጠገቡ፤ መካኒቱ ሰባት ወልዳለችና፥ ብዙም የወለደችው መውለድ አልቻለችም። 6 እግዚአብሔር ይገድላል፤ ያድናልም፤ ወደ ሲኦል ያወርዳል፤ ያወጣልም። 7 እግዚአብሔር ድሀ ያደርጋል፤ ባለጠጋም ያደርጋል፤ ያዋርዳል፤ ደግሞም ከፍ ከፍ ያደርጋል። 8 ችግረኛውን ከመሬት ያነሣዋል፤ ምስኪኑንም ከጕድፍ ያነሣዋል፤ ከሕዝቡ መኳንንት ጋር ያስቀምጠው ዘንድ፥ የክብርንም ዙፋን ያወርሰው ዘንድ። 9 ለሚጸልይ ጸሎቱን ይሰጠዋል፤ የጻድቃንን ዘመን ይባርካል፤ የሰው ኀይል ጽኑዕ አይደለምና። 10 እግዚአብሔር ጠላቶቹን ያደክማቸዋል፤ እግዚአብሔር ብቻ ቅዱስ ነው፤ ጥበበኛ በጥበቡ አይመካ፤ ኀይለኛም በኀይሉ አይመካ፤ ሀብታምም በሀብቱ አይመካ፤ የሚመካ ግን በዚህ ይመካ፤ እግዚአብሔርን በማወቅና በማስተዋል፤ በምድርም መካከል ፍርድንና እውነትን በማድረግ፥ እግዚአብሔር ወደ ሰማይ ወጣ፤ አንጐደጐደም። ጻድቅ እርሱ እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል፤ ለንጉሦቻችንም ኀይልን ይሰጣል፤ የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።” 11 በዚያም በእግዚአብሔር ፊት ተዉት። እነርሱም ወደ አርማቴም ወደ ቤታቸው ገቡ፤ ልጁም በካህኑ በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር። የካህኑ የዔሊ ልጆች ክፉ ሥራ 12 የካህኑም የዔሊ ልጆች ክፉዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አያውቁም ነበር። 13 መሥዋዕት በሚሠዉ በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ የነበረ የካህኑንም ሕግ አያውቁም ነበረ፤ ሕዝቡም ሁሉ መሥዋዕት በሠዉ ጊዜ የካህኑ ብላቴና ይመጣ ነበር፤ በእጁም ሦስት ጣት ያለው ሜንጦ ነበር፤ 14 ወደ ድስቱም ወይም ወደ ምንቸቱ ወይም ወደ አፍላሉ ወይም ወደ ቶፋው ይሰድደው ነበር። ሜንጦውም ያወጣውን ሁሉ ካህኑ ለእርሱ ይወስደው ነበር፤ በሴሎም ለእግዚአብሔር ሊሠዉ በሚወጡ በእስራኤላውያን ሁሉ ላይ እንዲህ ያደርጉ ነበር። 15 ደግሞም ስቡ ሳይጤስ የካህኑ ልጅ መጥቶ የሚሠዋውን ሰው፥ “ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ አይወስድምና እጠብስለት ዘንድ ለካህኑ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር። 16 የሚሠዋውም ሰው፥ “አስቀድሞ እንደ ሕጉ ስቡ ይጢስ፤ ኋላም ሰውነትህን ደስ የሚያሰኛትን ትወስዳለህ” ቢለው፥ እርሱ፥ “አይሆንም፥ ነገር ግን አሁን ስጠኝ፤ ካልሆነም በግድ አወስደዋለሁ” ይለው ነበር። 17 የእግዚአብሔርን ቍርባን ይንቁ ነበርና የዔሊ ልጆች ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረች። ብላቴናው ሳሙኤል በሴሎ 18 ሳሙኤል ግን ገና ብላቴና ሳለ የበፍታ ኤፉድ ታጥቆ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። 19 እናቱም ታናሽ መደረቢያ ሠራችለት፤ በየዓመቱም መሥዋዕት ለመሠዋት ከባልዋ ጋር ስትወጣ ትወስድለት ነበር። 20 ዔሊም ሕልቃናንና ሚስቱን ባረካቸው፥ “ለእግዚአብሔር ስለ አገባኸው ስጦታ ፈንታ ከዚህች ሴት እግዚአብሔር ዘር ይስጥህ” አለው፤ እነርሱም ወደ ቤታቸው ገቡ። 21 እግዚአብሔርም ሐናን ጐበኘ፤ ዳግመኛም ፀነሰች፥ ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆችን ወለደች። ብላቴናው ሳሙኤልም በእግዚአብሔር ፊት አደገ። ካህኑ ዔሊ የልጆቹን ክፉ ሥራ እንደ ሰማ 22 ዔሊም እጅግ አረጀ፤ ልጆቹም የእስራኤልን ልጆች ያደረጓቸውን፥ በምስክሩ ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉት ሴቶችም ጋር እንደሚተኙ ሰማ። 23 እርሱም አላቸው፥ “ከእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ አፍ የምሰማውን ይህን ነገር ለምን ታደርጋላችሁ? 24 ልጆቼ ሆይ፥ ይህ አይሆንም፤ እኔ የምሰማው ይህ ነገር መልካም አይደለምና እንዲህ አታድርጉ። ሕዝቡንም እግዚአብሔርን ከማገልገል አትከልክሉአቸው። 25 ሰውስ ሰውን ቢበድል ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩለታል፤ ሰው ግን እግዚአብሔርን ቢበድል ስለ እርሱ ወደ ማን ይጸልዩለታል?” እነርሱ ግን እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ወድዶአልና የአባታቸውን ቃል አልሰሙም። 26 ብላቴናው ሳሙኤልም አደገ፤ በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሞገስ እያገኘ ሄደ። በካህኑ ቤተ ሰብ ላይ የተነገረ ትንቢት 27 የእግዚአብሔርም ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በግብፅ በፈርዖን ቤት ባሪያዎች ሳሉ ለአባትህ ቤት ተገለጥሁ፤ 28 ከእስራኤልም ነገድ ሁሉ ካህን ይሆነኝ ዘንድ፥ በመሠዊያዬም ላይ ይሠዋ ዘንድ፥ ዕጣንንም ያጥን ዘንድ፥ ኤፉድንም በፊቴ ይለብስ ዘንድ፥ የአባትህን ቤት ለእኔ መረጥሁት፤ የእስራኤልንም ልጆች የእሳት ቍርባን ሁሉ ስለ ምግብ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ። 29 በመሥዋዕቴ ላይና በዕጣኔ ላይ ስለ ምን በክፉ ዐይን ተመለከትህ? የእስራኤል ልጆች በፊቴ ከሚያቀርቡት መሥዋዕት ሁሉ በቀዳምያቱ ስለ አከበርሁህ ከእኔ ይልቅ ልጆችህን ለምን መረጥህ? 30 ስለዚህም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእውነት ቤትህ፥ የአባትህም ቤት፤ ለዘለዓለም በፊቴ እንዲኖር ተናግሬአለሁ፤ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ያከበሩኝን አከብራለሁና፥ የናቁኝም ይናቃሉና ይህ አይሆንልኝም። 31 እነሆ፥ ዘርህንም፥ የአባትህንም ቤት ዘር የማጠፋበት ዘመን ይመጣል፤ 32 በቤትህም ለዘለዓለም ሽማግሌ አይገኝም። 33 በዐይኖቹ የሚፈጽም በነፍሱም የሚተጋ ሰውን ከመሠዊያዬ አላጠፋም። ከቤትህ የሚቀሩት ሰዎች ሁሉ ግን በጐልማሶች ሰይፍ ይሞታሉ። 34 ይህ በሁለቱ ልጆችህ በአፍኒንና በፊንሐስ ላይ የሚመጣ ለአንተ ምልክት ነው፤ ሁለቱ በአንድ ቀን በጦር ይሞታሉ። 35 የታመነ ካህን ለእኔ አስነሣለሁ፤ በልቤም፥ በነፍሴም እንዳለ እንዲሁ ያደርጋል፤ እኔም የታመነ ቤት እሠራለታለሁ፤ ዘመኑን ሁሉ እኔ በቀባሁት ሰው ፊት ይሄዳል። 36 ከቤትህም የቀረው ሁሉ ይመጣል፤ ከካህናትም ወደ አንዲቱ ዕጣ፥ እንጀራ ወደምበላበት እባክህ ላከኝ ብሎ ለአንድ ብር መሐልቅ ለቍራሽ እንጀራ በፊቱ ይሰግዳል።” |