1 ነገሥት 2 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ዳዊት ለሰሎሞን የሰጠው ምክር 1 ዳዊትም የሚሞትበት ወራት ደረሰ፤ ልጁንም ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ 2 “እኔ የምድሩን መንገድ ሁሉ እሄዳለሁ፤ በርታ ሰውም ሁን፤ 3 እንደማዝዝህ የምታደርገውን ሁሉ ታውቅ ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ የተጻፈውን ሥርዐቱንና ትእዛዛቱን፥ ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ። 4 ይኸውም እግዚአብሔር ስለ እኔ፦ ‘ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በእውነት ቢሄዱ ከእስራኤል ዙፋን ሰው አይጠፋም’ ብሎ የተናገረውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው። 5 አንተም ደግሞ የሶርህያ ልጅ ኢዮአብ፥ ሁለቱን የእስራኤል ሠራዊት አለቆች የኔር ልጅ አበኔርን የኢያቴርንም ልጅ አሜሳይን ገድሎ፥ በእኔ ላይ ያደረገውን ታውቃለህ፤ የጦርነትንም ደም በሰላም አፈሰሰ፤ በወገቡም ባለው ድግና በእግሩም ባለው ጫማ ንጹሕ ደም አኖረ። 6 አንተም እንደ ጥበብህ አድርግ፤ ሽበቱንም በሰላም ወደ መቃብር አታውርደው። 7 ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ ቀርበውኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች ቸርነትን አድርግላቸው። በማዕድህም ከሚበሉት መካከል ይሁኑ። 8 የባውሬም ሀገር ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ እነሆ! በአንተ ዘንድ ነው፤ እኔም ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ ብርቱ ርግማን ረገመኝ፤ ከዚያም በኋላ ዮርዳኖስን በተሻገርሁ ጊዜ ሊቀበለኝ ወረደ፤ እኔም፦ ‘በሰይፍ አልገድልህም’ ብዬ በእግዚአብሔር ምየለታለሁ። 9 አንተ ግን ጥበበኛ ሰው ነህና ንጹሕ አታድርገው፤ የምታደርግበትንም አንተ ታውቃለህ፤ ሽበቱንም በደም ወደ መቃብር አውርደው” አለው። የንጉሥ ዳዊት ሞት 10 ዳዊትም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። 11 ዳዊትም በእስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። በኬብሮን ሰባት ዓመት፥ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። 12 ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ ጸና። የአዶንያስ መገደል 13 የአጊት ልጅ አዶንያስም ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ፤ ሰገደላትም፤ እርስዋም፥ “ወደ እኔ መምጣትህ በሰላም ነውን?” አለችው። እርሱም፥ “በሰላም ነው” አለ። 14 ደግሞም፥ “ከአንቺ ጋር ጉዳይ አለኝ” አለ፤ እርስዋም፥ “ተናገር” አለችው። 15 እርሱም፥ “መንግሥቱ ለእኔ እንደ ነበረ፥ እስራኤልም ሁሉ ንጉሥ እሆን ዘንድ ፊታቸውን ወደ እኔ አድርገው እንደ ነበረ አንቺ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖለታልና መንግሥት ተመልሳ ለወንድሜ ሆናለች። 16 አሁንም አንዲት ልመና እለምንሻለሁ ፤ ፊትሽንም አትመልሺብኝ” አላት። እርስዋም፥ “ተናገር” አለችው፤ 17 እርሱም፥ “ፊቱን አይመልስብሽምና፥ ሱነማዪቱን አቢሳን ይድርልኝ ዘንድ ለንጉሡ ለሰሎሞን እንድትነግሪው እለምንሻለሁ” አለ። 18 ቤርሳቤህም፥ “መልካም ነው፤ ስለ አንተ ለንጉሡ እነግረዋለሁ” አለች። 19 ቤርሳቤህም የአዶንያስን ነገር ትነግረው ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ገባች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ ሳማትም፤ በዙፋኑም ተቀመጠ፤ ለንጉሡም እናት ወንበር አስመጣላት፤ በቀኙም ተቀመጠች። 20 እርስዋም፥ “አንዲት ትንሽ ልመና እለምንሃለሁ፤ ፊትህን አትመልስብኝ” አለች። ንጉሡም፥ “እናቴ ሆይ! ፊቴን አልመልስብሽምና ለምኚ” አላት። 21 እርስዋም፥ “ሚስት ትሆነው ዘንድ ለወንድምህ ለአዶንያስ ሱነማዪቱ አቢሳን ይስጡት” አለች። 22 ንጉሡም ሰሎሞን ለእናቱ መልሶ፥ “ሱነማዪቱን አቢሳን ለአዶንያስ ለምን ትለምኚለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ነውና መንግሥትን ደግሞ ለምኚለት፤ ካህኑም አብያታርና የሶርህያ ልጅ የጭፍሮች አለቃ ኢዮአብ ደግሞ ከእርሱ ጋር ናቸው” አላት። 23 ንጉሡም ሰሎሞን፦ እንዲህ ሲል በእግዚአብሔር ማለ። “አዶንያስ ይህን ቃል በሕይወቱ ላይ እንደ ተናገረ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ይህንም ይጨምርብኝ። 24 አሁንም ያጸናኝ፥ በአባቴም በዳዊት ዙፋን ላይ ያስቀመጠኝ፥ እንደ ተናገረውም ቤትን የሠራልኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ዛሬ አዶንያስ ፈጽሞ ይገደላል። 25 ንጉሡም ሰሎሞን የዮዳሄን ልጅ በናያስን ላከ፤ እርሱም አረደው፤ ያንጊዜም አዶንያስ ሞተ። የአብያታር መሻርና የኢዮአብ መገደል 26 ንጉሡም ካህኑን አብያታርን፥ “አንተ ዛሬ የሞት ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፥ አባቴም የተቀበለውን መከራ ሁሉ አንተ ስለ ተቀበልህ አልገድልህምና በዓናቶት ወዳለው ወደ እርሻህ ፈጥነህ ሂድ” አለው። 27 በሴሎም በዔሊ ቤት ላይ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አወጣው። 28 ለሶርህያ ልጅ ለኢዮአብም ወሬ ደረሰለት፤ ኢዮአብ ከአዶንያስ ጋር ተባብሮ ተከተለው እንጂ ከሰሎሞን ጋር አልተባበረም፤ አልተከተለውምም ነበርና። ኢዮአብም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ። 29 ንጉሡም ሰሎሞን ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ እንደ ያዘ ሰማ፤ ንጉሥ ሰሎሞንም ወደ ኢዮአብ እንዲህ ሲል ላከ፤ “በመሠዊያው ቀንድ የተማጠንህ ምን ሆነህ ነው?” ኢዮአብም፥ “ፈርቼሃለሁና በእግዚአብሔር ተማጠንሁ” አለ። ሰሎሞንም የዮዳሄን ልጅ በንያስን ልኮ፥ “ሂድ ግደልና ቅበረው” ብሎ አዘዘው። 30 የዮዳሄ ልጅ በንያስም ወደ ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን መጥቶ፥ “ንጉሡ፦ ውጣ ይልሃል” አለው፤ ኢዮአብም፥ “በዚህ እሞታለሁ እንጂ አልወጣም” አለ። የዮዳሄ ልጅ በንያስም፦ ተመልሶ “ኢዮአብ የተናገረው ቃል፥ የመለሰልኝም እንዲህ ነው” ብሎ ለንጉሡ ነገረው። 31 ንጉሡም አለው፥ “ሂድና እንደ ነገረህ አድርግ፤ ገድለህም ቅበረው፤ ኢዮአብም በከንቱ ያፈሰሰውን ደም ከእኔና ከአባቴ ቤት ታርቃለህ። 32 አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእርሱ የሚሻሉትን ሁለቱን ጻድቃን ሰዎች፥ የእስራኤልን ሠራዊት አለቃ የኔርን ልጅ አበኔርን፥ የይሁዳንም ሠራዊት አለቃ የኢያቴርን ልጅ አሜሳይን በሰይፍ ገድሎአልና እግዚአብሔር የዐመፅ ደሙን በራሱ ላይ መለሰ። 33 ደማቸውም በኢዮአብ ራስና በዘሩ ራስ ላይ ለዘለዓለም ይመለስ፤ ለዳዊት ግን ለዘሩና ለቤቱ፥ ለዙፋኑም የእግዚአብሔር ሰላም ለዘለዓለም ይሁን።” 34 የዮዳሄም ልጅ በንያስ ወጥቶ ያዘው፤ ገደለውም፤ በምድረ በዳም ባለው በራሱ ቤት ቀበረው። 35 ንጉሡም በእርሱ ፋንታ የዮዳሄን ልጅ በንያስን የሠራዊቱ አለቃ አድርጎ ሾመ፤ መንግሥቱም በኢየሩሳሌም ጸናች። በአብያታርም ፋንታ ካህኑን ሳዶቅን ሾመ። የሳሚ መገደል 36 ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራውና እንዲህ አለው፥ “በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ወዲህና ወዲያም አትውጣ። 37 በምትወጣበትና የቄድሮንንም ፈፋ በምትሻገርበት ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ፤ ደምህም በራስህ ላይ ይሆናል።” ያንጊዜም ንጉሡ አማለው። 38 ሳሚም ንጉሡን፥ “ጌታዬ ንጉሥ የተናገርኸው ቃል መልካም ነው፤ አገልጋይህም እንዲሁ ያደርጋል” አለው፤ ሳሚም በኢየሩሳሌም ሦስት ዓመት ተቀመጠ። 39 ከሦስት ዓመትም በኋላ ከሳሚ አገልጋዮች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ለሳሚም፥ “እነሆ፥ አገልጋዮችህ በጌት ናቸው” ብለው ነገሩት። 40 ሳሚም ተነሣ፤ አህያውንም ጭኖ አገልጋዮቹን ይሻ ዘንድ ወደ ጌት ወደ አንኩስ ዘንድ ሄደ፤ ሳሚም ሄዶ አገልጋዮቹን ከጌት አመጣ። 41 ሰሎሞንም ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ አገልጋዮቹን እንዳመጣ ሰማ። 42 ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራና፥ “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ለመሄድ በምትወጣበት ቀን ፈጽመህ እንድትሞት ዕወቅ ብዬ በእግዚአብሔር አላስማልሁህምን? ወይስ አላስመሰከርሁብህምን? 43 የእግዚአብሔርን መሐላ፥ እኔም ያዘዝሁትን ትእዛዝ ስለምን አልጠበቅህም?” አለው። 44 ንጉሡም ደግሞ ሳሚን፥ “አንተ በአባቴ በዳዊት ላይ የሠራኸውን፥ ልብህም ያሰበውን ክፋት ሁሉ ታውቃለህ፤ እግዚአብሔርም ክፋትህን በራስህ ላይ ይመልሳል። 45 ንጉሡ ሰሎሞን ግን የተባረከ ይሆናል፤ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘለዓለም ይጸናል” አለው። 46 ሰሎሞንም የዮዳሄን ልጅ በንያስን አዘዘው፤ ወጥቶም ገደለው። የሰሎሞንም መንግሥት በኢየሩሳሌም ጸና። |