1 ነገሥት 15 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)የይሁዳ ንጉሥ አብያ ( 2ዜ.መ. 13፥1—14፥1 ) 1 የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት የሮብዓም ልጅ አብያ በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። 2 በኢየሩሳሌምም ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። 3 ከእርሱም አስቀድሞ ባደረገው በአባቱ ኀጢአት ሁሉ ሄደ፤ ልቡም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አልነበረም። 4 ነገር ግን ልጁን ከእርሱ በኋላ ያስነሣ ዘንድ፥ ኢየሩሳሌምንም ያጸና ዘንድ አምላኩ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት በኢየሩሳሌም መብራትን አደረገለት፤ 5 ከኬጥያዊው ከኦርዮ ነገር በቀር ዳዊት በዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አድርጎ ነበርና፥ ካዘዘውም ነገር ሁሉ ፈቀቅ አላለም ነበርና። 6 በኢዮርብዓምና በሮብዓም መካከል በዘመናቸው ሁሉ ጠብ ነበረ። 7 የቀረውም የአብያ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ እነሆ፥ የተጻፈ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብአም መካከል ሰልፍ ነበረ። 8 ኢዮርብዓም በነገሠ በሃያ አራተኛ ዓመቱ አብያ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት። ልጁም አሳ በፋንታው ነገሠ። 9 በእስራኤልም ንጉሥ በኢዮርብዓም በሃያ አራተኛው ዓመት አሳ በይሁዳ ላይ ነገሠ። 10 በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሐና የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። 11 አሳም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ። 12 ከሀገሩም የጣዖታትን ምስል ሁሉ አስወገደ፥ አባቶቹም የሠሩአቸውን ጣዖታትን ሁሉ አጠፋ። 13 የማምለኪያ ዐፀድ ጣዖታትን ስለ ሠራች እናቱን ሐናን እቴጌ እንዳትሆን ሻራት፤ አሳም የማምለኪያ ዐፀዱን አስቈረጠው፥ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ በእሳት አቃጠለው። 14 ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ የአሳ ልብ ግን በዘመኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ነበረ። 15 አባቱ የቀደሰውንና እርሱም የቀደሰውን ወርቅና ብር፥ ዕቃውንም ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባው። 16 አሳና የእስራኤል ንጉሥ ባኦስ በዘመናቸው ሁሉ ሲዋጉ ኖሩ። 17 የእስራኤልም ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፤ ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ዘንድ ማንም እንዳይወጣ ወደ እርሱም ማንም እንዳይገባ አድርጎ ራማን ሠራት። 18 አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሥ ቤተ መዛግብት የተገኘውን ብርና ወርቅ ሁሉ ወስዶ ለአገልጋዮቹ ሰጣቸው፤ ንጉሡም አሳ በደማስቆ ለተቀመጠው ለአዚን ልጅ ለጤቤርማን ልጅ ለሶርያ ንጉሥ ለወልደ አዴር፥ 19 “በእኔና በአንተ መካከል በአባቴና በአባትህ መካከል ቃል ኪዳን ጸንቶአል፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ገጸ በረከት ልኬልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ” ብሎ ላከ። 20 ወልደ አዴርም ለንጉሡ ለአሳ እሺ አለው፤ የሠራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰድዶ ኢናንንና ዳንን፥ አቤልቤትመዓካንና ኬኔሬትን ሁሉ የንፍታሌምንም ሀገር ሁሉ መታ። 21 ባኦስም ያን በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ትቶ ወደ ቴርሳ ተመለሰ። 22 ንጉሡም አሳ በይሁዳ ሁሉ ላይ አዋጅ ነገረ፤ ማንም ነጻ አልነበረም፥ ንጉሡ ባኦስም የሠራበትን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰደ፤ የይሁዳም ንጉሥ አሳ የብንያምንና የመሴፋን ኮረብታ ሠራበት። 23 የቀረውም የአሳ ነገር ሁሉ ብርቱ ሥራዎቹም ሁሉ፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥት ታሪክ የተጻፈ አይደለምን? ነገር ግን በሸመገለ ጊዜ እግሮቹ ታመሙ። 24 አሳም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም ኢዮሣፍጥ በፋንታው ነገሠ። 25 በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሁለተኛው ዓመት የኢዮርብዓም ልጅ ናባጥ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ በእስራኤልም ላይ ሁለት ዓመት ነገሠ። 26 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ በአባቱም መንገድ እስራኤልንም ባሳተበት ኀጢአት ሄደ። 27 ከበለዓን ቤት የሆነ የአኪያ ልጅ ባኦስ ዐመፀበት፤ ናባጥና እስራኤልም ሁሉ ገባቶንን ከብበው ነበርና ባኦስ በፍልስጥኤልም ሀገር ባለው በገባቶን ገደለው። 28 በይሁዳ ንጉሥ በአሳ በሦስተኛው ዓመተ መንግሥት ባኦስ ናባጥን ገደለው፥ በፋንታውም ነገሠ። 29 ከነገሠም በኋላ የኢዮርብዓምን ወገን ሁሉ አጠፋ፥ በባሪያው በሴሎናዊው በአኪያ እጅ እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ እስኪያጠፋው ድረስ ከኢዮርብዓም ወገን ሕይወት ያለውን አላስቀረም። 30 ይኸውም ኢዮርብዓም ስለ ሠራው ኀጢአት፥ እስራኤልንም ስላሳተበት፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ስላስቈጣበት ማስቈጣት ነው። 31 የቀረውም የናባጥ ነገርና ያደረገውም ሁሉ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 32 በአሳና በእስራኤል ንጉሥ በባኦስ መካከል በዘመናቸው ሁሉ ጦርነት ነበረ። 33 በይሁዳም ንጉሥ በአሳ በሦስተኛው ዓመት የአኪያ ልጅ ባኦስ በእስራኤል ሁሉ ላይ በቴርሣ ንጉሥ ሆኖ ሃያ አራት ዓመት ነገሠ። 34 በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፥ በናባጥም ልጅ በኢዮርብዓም መንገድ እስራኤልንም ባሳተበት ኀጢአት ሄደ። |