ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 9 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 “ከዚህ በኋላ ወደ ጫጕላው በገባ ጊዜ ወድቆ ሞተ። 2 ከዚህ በኋላም ፋናችንንና መብራታችንን አጠፋን፤ እናለቅስ ዘንድም ተቀመጥን፤ ያገሬ ሰዎችም ሁሉ ተነሥተው ይመክሩኝና ያረጋጉኝ ጀመሩ፤ ከዚህም በኋላ እስከ ማግሥትዋ ቀን ሌሊት ድረስ ዝም አልሁ። 3 ከዚህ በኋላ ሁሉም ዝም ባሉ ጊዜ፥ እኔንም መምከር በተዉ ጊዜ እኔ ሌሊት ተነሥቼ ሸሸሁ፤ ወደዚህም ምድረ በዳ መጣሁ። 4 ለዘለዓለሙ በዚሁ እኖራለሁ እንጂ እንግዲህ ወዲህ ወደ ሀገሬ እንዳልመለስ ቈረጥሁ፤ ሁልጊዜ እጾማለሁ፤ እስክሞትም ድረስ አለቅሳለሁ እንጂ እህል አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም።” 5 ያ የማስበው አሳቤም ተወኝ፤ እኔም መለስሁላት፤ እንዲህም አልኋት፦ 6 “ከሴቶች ሁሉ አንቺ አላዋቂ ነሽ፤ ያገኘችንን የእኛን ልቅሶ አታዪምን? 7 ስለ ሁላችን እናት ስለ ጽዮን ሁላችን በኀዘን አለን፤ መከራንም ፈጽመን ተቀበልን። 8 አሁንም በእውነት ታዝኚና ታለቅሺ ዘንድ ይገባሻል፤ እኛ ሁላችንም ያዘንን ነንና፤ እኛም ስለ ብዙዎች እናዝናለን፤ አንቺ ግን ስለ አንዱ ልጅሽ ታዝኛለሽ። 9 ምድርን ጠይቂአት፤ ትነግርሻለችም፤ በእርስዋ ላይ ይህን ያህል ስለ ተወለዱት ታለቅስ ዘንድ አግባብ ለእርስዋ ነው። 10 ሁሉም ከጥንት ጀምሮ በእርስዋ ላይ ተፈጠሩ። እነሆም ሌሎች መጥተው ሁሉንም በሙሉ ፈጽሞ ለማጥፋት ወሰዷቸው። 11 እንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ ያለቅስ ዘንድ የሚገባው ማን ነው? ይህን ያህል ብዙ የጠፋበት ነውን? ወይስ አንቺ ስለ አንድ ልጅሽ ታዝኛለሽን? 12 ወይስ በጻዕርና በገዓር የወለድሁትን ልጄን አጥቻለሁና፤ የእኔ ልቅሶ እንደ ምድር ልቅሶ አይደለም ትያለሽን? 13 ምድር ግን ብዙ አሕዛብ ወደ እርሷ እንደ መጡ እንደዚሁ ሄዱ። 14 ነገር ግን እኔ እንዲሁ እልሻለሁ፤ አንቺ አምጠሽ እንደ ወለድሽ እንዲሁም ምድር ከጥንት ጀምሮ በእርሷ ለተፈጠሩ ሰዎች ፈጣሪዋ የሰጣትን ፍሬዋን ሰጠቻቸው። 15 አሁንም ይህን ኀዘንሽን ካንቺ አርቂ፤ ስለ አገኘችሽ ቅጣትና መከራም ትዕግሥተኛ ሁኚ። 16 እግዚአብሔርን ብታመሰግኚው ይረዳሻልና፥ ልጅሽንም በጊዜው ታገኚዋለሽና፥ በሴቶችም ዘንድ መከራን የታገሠች ትባያለሽና፥ 17 አሁንም ወደ ሀገርሽ ግቢ፤ ወደ ባልሽም ሂጂ።” 18 እርስዋም አለችኝ፥ “እንዲህስ አላደርግም፤ በዚህ እሞታለሁ እንጂ ወደ ሀገሬ አልገባም።” 19 ዳግመኛም ተናገርኋት፤ እንዲህም አልኋት፦ 20 “ይህን ነገር አታድርጊ፤ እሺ በዪኝ፤ ራስሽንም እንደ ጽዮን መከራ አድርጊ፤ ስለ ኢየሩሳሌምም ከተማ ተረጋጊ። 21 ቤተ መቅደሳችን እንደ ፈረሰ፥ መሠዊያችን እንደ ተሰባበረ አታዪምን? 22 ግናያቱ እንደ ጠፋ፥ ምስጋናችን እንደ ቀረ፥ ዘመራ ዘውዳችን እንደ ወደቀ፥ የመቅረዛችን መብራት እንደ ጠፋ፥ የቃል ኪዳናችን ታቦት እንደ ተማረከች፥ ንዋየ ቅድሳታችን እንዳደፈ፥ ስማችን እንደ ረከሰ፥ ጌቶቻችን እንደ ተዋረዱ፥ ካህኖቻችን እንደ ተቃጠሉ፥ ሌዋውያኖቻችን እንደ ተማረኩ፥ ደናግሎቻችን እንደ ተገደሉ፥ ሚስቶቻችንን እንደ ቀሙን፥ ጻድቃኖቻችን እንደ ተጐተቱ፥ ጐልማሶቻችን እንደ ተገዙ፥ ወንዶች ልጆቻችን እንደ ተቀሙ፥ አርበኞቻችን እንደ ደከሙ አታዪምን? 23 ከዚህ ሁሉ የሚበልጥ ጽዮን ጠፋች፤ ክብርዋም ከእርስዋ ወጣ፤ በጠላቶቻችንም እጅ ወደቅን። 24 አንቺም ተዪ፥ ልዑልና ኀያል ይቅር ይልሽ ዘንድ፥ ከድካምሽም እግዚአብሔር ፈጽሞ ያሳርፍሽ ዘንድ ይህን ብዙ ኀዘንሽን አርቂ።” 25 ከዚህ በኋላ ይኽን ስናገራት ድንገት ፊትዋ ከፀሐይ ይልቅ በራ፤ መልኳም እንደ መብረቅ አንጸባረቀ፤ ወደ እርሷ መቅረብንም ፈራሁ፤ ልቡናዬም ደነገጠብኝ፤ ከዚህም በኋላ ይህ ምን እንደ ሆነ ሳስብ አስደነገጠችኝ። 26 በታላቅ ድምፅም ጮኸች፤ ከድምፅዋም የተነሣ ምድር እስክትነዋወጥ ድረስ ድምፅዋ እጅግ የሚያስፈራ ሆነ። 27 ባየኋትም ጊዜ እነሆ የከበረችና የታነጸች ከተማ ነበረች እንጂ ሴት አልነበረችም፤ ታላቅ የሆነ የመሠረቶችዋንም ቦታ አየሁ፤ ፈርቼም በታላቅ ድምፅ ጮህኹ። እንዲህም አልሁ፦ 28 “አስቀድሞ ወደ እኔ የመጣህ መልአኩ ዑርኤል፥ አንተ ወዴት ነህ? ወደ ብዙ ምርምር እገባ ዘንድ፥ ፍጻሜዬም ለጕስቍልናዬ ትሆን ዘንድ፥ ጸሎቴም ለተግዳሮት ይሆን ዘንድ እንዲህ ለምን አደረግኸኝ?” የራእዩ ትርጓሜ 29 እኔ እንደዚህ ስናገር እነሆ፥ ቀድሞ ወድ እኔ የመጣው ያ መልአክ ወደ እኔ መጣ። 30 እንደ ሬሳ ተኝቼ አገኘኝ፤ አእምሮዬም ከእኔ ጋር አልነበረም፤ ቀኝ እጄንም ይዞ አጸናኝ፤ በእግሮችም አቅንቶ አቆመኝ። 31 መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ምን ሆንህ? ምንስ ያስደነግጥሃል? ልብህስ ካንተ ጋር ስለምን የለም?” 32 እኔም አልሁት፥ “አንተ ጥለኸኛልና፥ ተለይተኸኛልምና፥ እኔ እንደ ነገርኸኝ ወደዚህ ምድረ በዳ መጣሁ፤ ወደዚህም ምድረ በዳ በመጣሁ ጊዜ እነሆ፥ ማወቅ የማይቻለኝን አየሁ።” 33 እርሱም አለኝ፥ “እንግዲህስ እነግርህ ዘንድ እንደ ሰው ቁም።” 34 እኔም አቤቱ ተናገር አልሁት፥ “ድንገት እንዳልሞት እንግዲህ አትለየኝ እንጂ። 35 ያላየሁትን አይቻለሁና፥ የማላውቀውንም ሰምቻለሁና። 36 ነገር ግን ምናልባት ልቡናዬ ይዘነጋ ይሆንን? ሰውነቴስ ትጨነቅ ይሆንን? 37 አሁንም አቤቱ በጅ በለኝ፤ የዚህንም ራእይ ትርጓሜ ለባሪያህ ንገረው።” 38 እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ስለምትፈራው ነገር አስተምርህ ዘንድ ስማኝ። ይህ የተሰወረ ምሥጢር ስለሆነ፦ ልዑል እግዚአብሔር ገልጦልሃልና። 39 ጽድቅህንም አየ፤ ስለ ወገኖችህ ብዙ ታዝናለህና፤ ስለ ጽዮንም እጅግ ትቈረቈራለህና። 40 ነገሩ ይህ ነው፦ 41 ቀድሞ እንደ አልቃሽ ሆና ያየሃት፥ ታረጋጋትም ዘንድ የጀመርህ ይች ሴት፥ 42 አሁን አንተ እንዳየሃት ሴት አይደለችም። የታነጸች ከተማ እንጂ። 43 ስለ ልጅዋ መከራ ነግራሃለችና። 44 ያች ያየሃት ሴት ዛሬ እንደ ታነጸች ከተማ ሀገር ሁና የምታያት ጽዮን ናት። 45 ሠላሳ ዘመን መካን ሆንኹ ያለችህም ይህ ነው፤ የሚያቀርቡት መሥዋዕት ሳይኖር ዓለም ሦስት ሺህ ዘመን ኖሯልና። 46 ከሦስት ሺህ ዓመት በኋላም ሰሎሞን ከተማን ሠራ፤ ያንጊዜም ቍርባንን አቀረበ። ያችም መካን ሴት የወለደችው ልጅ፥ 47 ይህም በብዙ ድካም አሳደግሁት ያለችህ ኢየሩሳሌም የኖረችው ዘመን ነው። 48 ይህም ልጅዋ ወደ ጫጕላው በገባ ጊዜ ወድቆ ሞተ፤ ይህም መከራ አገኘን ያለችህ የኢየሩሳሌም ጥፋትዋ ነው። 49 እነሆ ለልጆችዋ እንዴት እንደምታለቅስላቸው ያየሃት፥ አንተም ከመከራዋ ታረጋጋት ዘንድ የጀመርህ ያች ሴት ኢየሩሳሌም ናት። 50 አሁንም ልዑል እግዚአብሔር ስለ እርስዋ በፍጹም ሰውነትህ እንድታዝን፥ በፍጹም ልቡናህም እንድትቈረቈር ባየ ጊዜ የደስታዋን ጌጥና የክብሩዋን መገለጥ አሳየህ። የተሰወረ ምሥጢር ነውና። 51 ስለዚህ ነገር ቤት ባልተሠራበት በዚህ በምድረ በዳ ትኖር ዘንድ እነግርሃለሁ። 52 ልዑል እግዚአብሔር ያሳይህ ዘንድ ያለውን ሁሉ አውቄአለሁና። 53 ስለዚህም የግንብ መሠረት ወደሌለበት ወደዚህ ትመጣ ዘንድ እነግርሃለሁ። 54 ልዑል ይገለጥበት ዘንድ ባለው ቦታ የሰው ሥራ ግንብ ሊኖር አይቻልምና። 55 “አንተስ እንግዲህ አትፍራ፤ ልብህም አይደንግጥ፤ ገብተህ ብርሃንዋንና የግንብዋን ጽናት እይ እንጂ። 56 መስማት የምትችለውን ያህል በጆሮህ ስማ። 57 አንተ ከብዙዎች ይልቅ ራስህን ብፁዕ አሰኝተሃልና፥ በልዑልም ዘንድ እንደ ጥቂቶች ተጠርተሃልና። 58 ዛሬም በዚህ እደር። 59 ልዑል እግዚአብሔር በዓለም በሚኖሩ ሰዎች ላይ በጊዜው የሚያደርገውን ራእይ ነገ በሕልም ያሳይሃል።” 60 በዚያችም ሌሊት፥ በማግሥቱም እንዳዘዘኝ አደርሁ። |