ይህ መፅሐፍ በእግዚአብሔር አልተነፀረም እና የክርስቲያን ካኖን ወይም የአይሁድ ታናክ ክፍል አይደለም። ለታሪክና ለጥናት ዓላማ ብቻ ይታያል። ሙሉ ማብራሪያን ይመልከቱ መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 10 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በንስር አምሳል ያየው አምስተኛው ራእይ 1 ከዚህም በኋላ በማግሥቱ ሌሊት ንስር ከባሕር ሲወጣ በሕልም አየሁ፤ ክንፎቹም ዐሥራ ሁለት ናቸው፤ ራሶቹም ሦስት ናቸው። 2 በክንፎቹም በዓለሙ ሁሉ ይበርራል፤ የሰማይ ነፋሳትም ሁሉ ይነፍሱበታል፤ ደመናትም በእርሱ ይሰበሰባሉ። 3 ከእነዚያም ክንፎች ራሶች ይበቅላሉ፤ እነዚያም ራሶች ደቃቅና ታናናሽ ክንፍ ይሆናሉ፤ 4 ራሶቹም ዝም ይላሉ፤ ከእነዚያም ራሶች መካከለኛው ራስ ይበልጣል፤ ነገር ግን እርሱም ከእነርሱ ጋር ዝም ይላል። 5 ያም ንስር ምድርንና በምድር የሚኖሩትን ይገዛ ዘንድ በክንፎቹ ይበርራል፤ 6 ከሰማይ በታች ያለ ሁሉ ይገዛለት ዘንድ ያን ንስር በምድር ከተፈጠረው ፍጥረት የሚከራከረው ማንም የለም። 7 ከዚህ በኋላ ያ ንስር ተነሣ፤ በጥፍሮቹም ቆመ፤ በታላቅ ድምፅም ጮኸ፤ ክንፎቹንም እንዲህ አላቸው፦ 8 “በየቦታችሁ ተኙ እንጂ ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ በአንድነት አትነሡ፤ በየጊዜውም ትነሣላችሁ። 9 የኋለኛዪቱ ራሱም ከሁሉ ትበልጣለች።” 10 ባየሁ ጊዜም ድምፁ የሚወጣ ከሥጋው መካከል እንጂ ከራሱ ውስጥ አይደለም። 11 የእነዚያ ራሶች ቍጥሮችም ስምንት ናቸው። 12 ከዚህ በኋላ በቀኝ በኩል ክንፍ ወጣ፤ ምድሩንም ሁሉ ገዛ። 13 ከዚህ በኋላ ጥፋቱ በደረሰ ጊዜ ቦታው እስከማይታይ ድረስ እርሱም ጠፋ፤ ሁለተኛውም ወጣ፤ እርሱም ብዙ ዘመን አጽንቶ ገዛ። 14 ከዚህም በኋላ ጥፋቱ በደረሰ ጊዜ እርሱም እንደ ፊተኛው ጠፋ። 15 ቃልም መጣለት፤ እንዲህም አለው፦ 16 “ምድርን ይህን ያህል ዘመን አጽንተህ የምትገዛ አንተ ንስር ሳትጠፋ ይኽን የምነግርህን ስማ። 17 ከአንተ በኋላ እንደ አንተ የሚጸና፥ የእኩሌታህንም ያህል የሚገዛ የለም።” 18 ሦስተኛውም ወጣ፤ እርሱም እንደ መጀመሪያው አጽንቶ ገዛ፤ ከዚህ በኋላ እርሱም ጠፋ። 19 ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ክንፎቹ ሁሉ ወጡ፤ እያንዳንዳቸውም ገዙ፤ ዳግመኛ ሁሉም ጠፉ። 20 ከዚህ በኋላ ክንፎቹ አጽንተው ይገዙ ዘንድ በግራ በኩል በየጊዜያቸው ተነሡ፤ ነገር ግን ፈጥነው ጠፉ። 21 ከእነርሱም ውስጥ የተነሡ አሉ፤ ነገር ግን እነርሱ አልገዙም። 22 ከዚህ በኋላም እነዚያ ዐሥራ ሁለቱ ክንፎቹ ጠፉ፤ እኒያም ሁለቱ ራሶቹ ጠፉ። 23 ዝም ከሚሉ ከሦስቱ ራሶቹና ከስድስቱ ራሶቹ በቀር ከዚህ ንስር ወገን የቀረ የለም። 24 ከዚህም በኋላ ከእነዚያ ከስድስቱ ራሶች ሁለቱ ተለይተው ሄዱ፤ በቀኝ በኩል ባለ ራሱ ውስጥም ተቀመጡ፤ አራቱ ግን በቦታቸው ቀሩ። 25 እኒህ አራቱ ራሶች ግን ይቆሙ ዘንድ፥ እነርሱም ይገዙ ዘንድ ተማከሩ። 26 ከዚህም በኋላ አንዱ ተነሥቶ ቆመ፤ ነገር ግን ፈጥኖ ጠፋ። 27 ሁለተኛውም እንዲሁ ከፊተኛው ይልቅ እርሱ ፈጥኖ ጠፋ። 28 ከዚህ በኋላ የቀሩት እኒህ ሁለቱ ተተክተው ይገዙ ዘንድ እንዲሁ ተማከሩ። 29 ከዚህም በኋላ እኒህ ሲማከሩ ዝም ከሚሉ ከሦስቱ ራሶች መካከለኛ የሚሆን አንዱ ተነሣ፤ ከእነርሱም የሚበልጥ እርሱ ነው። 30 ከዚህም በኋላ እኒህን ሁለቱን ራሶች ከእርሱ ጋር ወሰዳቸው። 31 ያም ራስ አብረውት ካሉት ጋራ ተመለሰ፤ ይገዙ ዘንድ የተማከሩ እኒህን ሁለቱንም ራሶች ዋጣቸው። 32 ያም ራስ ምድርን ሁሉ ያዛት፤ በውስጥዋም የሚኖሩትን በብዙ ድካምና መከራ አሠቃያቸው፤ ከቆሙት ከእኒያ ክንፎች ሁሉ ይልቅ ፈጽሞ ዓለምን ቀማ። 33 ከዚህም በኋላ መካከለኛው ራስ እንደ እነዚያ ጠፋ። 34 ሁለቱ ራሶችም ቀሩ፤ እነርሱም እንዲሁ ምድርንና በውስጧ የሚኖሩትን ገዙ። 35 ከዚህ በኋላ ያ በቀኝ በኩል ያለው ራስ በግራ በኩል ያለውን ዋጠው። ከዱር የወጣ አንበሳ 36 “ወደ ፊትህ ተመልከት፤ የምታየውንም ዕወቅ” የሚለኝን ቃል ሰማሁ። 37 ባየሁም ጊዜ እነሆ አንበሳ እያገሣ ከዱር ተነሣ፤ እንደ ሰውም ድምፅ ሲናገር ሰማሁት፤ ያንም ንስር እንዲህ አለው፦ 38 “የምነግርህንና ልዑል ያለህን አንተ ስማ። 39 ምድርን ይገዟት ዘንድ ከፈጠርኋቸው፥ የዘመንም ፍጻሜ ከሚደርስባቸው ከእነዚያ ከአራቱ እንስሳ የቀረህ አንተ አይደለህምን?” 40 አራተኛውም መጥቶ ያለፉትን በብዙ ድካምና ሕማም ይህን ዓለም የቀሙትን እነዚያን እንስሳ ሁሉ ድል ያደርጋቸዋል፤ ይህን ያህል ዘመን በዚህ ዓለም በተንኰል ኖረ። 41 ዓለምንም በክፉ አገዛዝ ገዛት። 42 ጻድቃንን ቀምቶአቸዋልና፥ ደጋጎቹንም በድሎአቸዋልና፥ ቅኖቹንም ጠልቶአቸዋልና፥ አሰተኞቹንም ወዶአቸዋልና፥ የጻድቃንንም አንባቸውን አፍርሶአልና፥ ያልበደሉትንም ቅጽራቸውን አፍርሶአልና። 43 ኀጢአቱም ወደ ልዑል ደርሳለችና፥ ትዕቢቱም ወደ ኀያል ደርሳለችና። 44 ልዑልም የራሱን ሰዎች ተመልክትዋቸዋልና፥ እነሆም ዓመቱ ተፈጽሞአልና። 45 ስለዚህም አንተ ንስር ፈጽመህ ትጠፋለህ፤ ኀጢአተኞች ክንፎችህ፥ ዝንጉዎች ራሶችህ፥ ክፉዎች ጥፍሮችህና ዐመፀኛው ሥጋህ ይጠፋሉ። 46 ምድርም ከመከራዋ ሁሉ እፎይ ብላ ካንተ ፈጽማ ታርፍ ዘንድ የፈጣሪዋን ፍርዱንና ቸርነቱን ተስፋ ታደርጋለች። |