1 ቆሮንቶስ 8 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ለጣዖት የተሠዋውን መብላት ስለማይገባ 1 ለጣዖታት ስለሚሠዉ መሥዋዕቶች ሁላችንም ዕውቀት እንዳለን እናውቃለን፤ ዕውቀት ያስታብያል፤ ፍቅር ግን ያንጻል። 2 ዐወቅሁ የሚል ቢኖር፥ ሊያውቅ የሚገባውን ገና አላወቀም። 3 እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው ግን እርሱ በእርሱ ዘንድ በእውነት የታወቀ ነው። 4 ለጣዖታት የተሠዋውን ስለመብላት ግን ጣዖት ሁሉ በዓለም ከንቱ እንደሆነ፥ ከአንድ እግዚአብሔርም በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ እናውቃለን። 5 አማልክት የሚሉአቸው ነገሮች አሉና፤ በሰማይም ቢሆን፥ በምድርም ቢሆን፥ ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች ቢኖሩ፥ 6 ለእኛስ ሁሉ ከእርሱ የሆነ፥ እኛም ለእርሱ የሆን አንድ እግዚአብሔር አብ አለን፤ ሁሉ በእርሱ የሆነ፥ እኛም በእርሱ የሆን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም አለን። 7 ነገር ግን ሁሉ የሚያውቀው አይደለም፤ እስከ ዛሬ በጣዖታት ልማድ፥ ለጣዖት የተሠዋውን የሚበሉ አሉ፤ ኅሊናቸውም ደካማ ስለሆነ ይረክሳል። 8 መብል ግን ወደ እግዚአብሔር አያደርሰንም፤ ብንበላም አይረባንም፤ ባንበላም አይጎዳንም። 9 ነገር ግን እናንተን በማየት ሌላው እንዳይሰናከል ተጠንቀቁ። 10 አንተ አማኙ በጣዖት ቤት በማዕድ ተቀምጠህ ያየህ ቢኖር ያ ልቡ ደካማ የሆነ ሰው ወዲያው ለጣዖት የተሠዋውን ደፍሮ ይበላል። 11 ክርስቶስ ስለ እርሱ የሞተለት ያ ደካማ ወንድም አንተን በማየት ይጎዳል። 12 በባልንጀሮቻችሁ ላይ እንዲህ የምትበድሉ ከሆነ ደካማ ሕሊናቸውንም የምታቈስሉ ከሆነ ክርስቶስን ትበድላላችሁ። 13 ነገር ግን በመብል ምክንያት ወንድሜ የሚሰናከል ከሆነ ወንድሜን እንዳላሰናክል ለዘለዓለም ሥጋን አልበላም። |