1 ቆሮንቶስ 7 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)ስለ ጋብቻ 1 ስለ ጻፋችሁልኝስ ለሰው ወደ ሴት አለመቅረብ ይሻለዋል። 2 ነገር ግን እንዳትሴስኑ ሰው ሁሉ በሚስቱ ይወሰን፤ ሴትም ሁላ በባልዋ ትወሰን። 3 ለሚስትም ባልዋ የሚገባትን ያድርግላት፤ እንዲሁ ሚስትም ለባልዋ የሚገባውን ታድርግለት። 4 ሚስት በራስዋ አካል ሥልጣን የላትም፤ ሥልጣን ለባልዋ ነው እንጂ፤ እንዲሁም ባል በራሱ አካል ሥልጣን የለውም፤ ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ። 5 ለጸሎት እንድትተጉ ከምትስማሙበት ጊዜ ብቻ በቀር፥ ባልና ሚስት አትለያዩ፤ ዳግመኛ ሰይጣን ድል እንዳያደርጋችሁ በአንድነት ኑሩ፤ ሰውነታችሁ ደካማ ነውና ። 6 ይህንም የምላችሁ እንደ ፈቃድ ነው እንጂ፥ ላዝዛችሁ አይደለም። 7 ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ እግዚአብሔር እንደ አደለው ጸጋ ይኑር፤ ግብሩ እንዲህ የሆነ አለና፤ ግብሩ ሌላ የሆነም አለና። 8 ነገር ግን ያላገቡትንና አግብተው የፈቱትን እንደ እኔ ሆነው ቢኖሩ ይሻላቸዋል እላለሁ። 9 መታገሥ ባይችሉ ግን ያግቡ፤ በፍትወት ከመቃጠል ማግባት ይሻላልና። 10 ያገቡትንም በእግዚአብሔር ትእዛዝ አዝዛቸዋለሁ፤ በራሴ ትእዛዝም አይደለም፤ ሚስትም ከባልዋ አትፋታ። 11 ከተፋታችም ብቻዋን ትኑር፤ ያለዚያ ከባልዋ ጋር ትታረቅ፤ ባልም ሚስቱን አይፍታ። 12 ሌላውን ግን ከራሴ እናገራለሁ፤ ከጌታችንም አይደለም፤ ከወንድሞቻችን መካከል የማታምን፥ ባልዋንም የምታፈቅር ከእርሱም ጋር ለመኖር የምትወድ ሚስት ያለችው ሰው ቢኖር ሚስቱን አይፍታ። 13 ሴቲቱም የማያምንና ሚስቱንም የሚያፈቅር ከእርስዋም ጋር ሊኖር የሚወድ ባል ቢኖራት ባልዋን አትፍታ። 14 የማያምን ባል በሚስቱ ይቀደሳልና፤ የማታምን ሚስትም በባልዋ ትቀደሳለችና፤ ያለዚያማ ልጆቻቸው ርኩሳን ይሆናሉ፤ አሁን ግን ቅዱሳን ናቸው። 15 የማያምን ግን ቢፈታ ይፍታ፤ ወንድምና እኅት እግዚአብሔር ለሰላም ስለ ጠራቸው እንደዚህ ላለ ግብር አይገዙምና። 16 ሚስትም ባልዋን ታድነው እንደ ሆነ አታውቅምና፤ ባልም ሚስቱን ያድናት እንደ ሆነ አያውቅምና። 17 ነገር ግን ሁሉ እግዚአብሔር እንደ አደለው፥ ሁሉም እግዚአብሔር እንደ ጠራው እንዲሁ ይኑር፤ ለአብያተ ክርስቲያናትም ሁሉ እንዲህ ሥርዐት እንሠራለን። 18 ተገዝሮ ሳለ የተጠራ ቢኖር አለመገዘርን አይመኝ፤ ያልተገዘረም ቢጠራ ከዚያ ወዲያ አይገዘር። 19 የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ መገዘርም አይጠቅምም፤ አለመገዘርም አይጎዳም። ወደ ሃይማኖት ስለ መጠራት 20 ሁሉ እንደ ተጠራ እንዲሁ ይኑር። 21 አንተ ባርያ ሳለህ ብታምን አያሳዝንህ፤ የሚቻልህ ከሆነ ግን ነጻነትህን አግኝ። 22 የተጠራ ባሪያ በእግዚአብሔር ዘንድ ነጻነት ያለው ነውና፤ እንዲሁ ነጻነት ያለውም ከተጠራ የክርስቶስ ባርያ ነው። 23 በዋጋ ገዝቶአችኋልና የሰው ተገዦች አትሁኑ። 24 ወንድሞቻችን ሁላችሁም በተጠራችሁበት እንዲሁ በእግዚአብሔር ኑሩ። ስለ ደናግልና ስለ መዓስባት 25 ስለ ደናግልም የምነግራችሁ የእግዚአብሔር ትእዛዝ አይደለም፤ ታማኝ እንድሆን እግዚአብሔር ይቅር ያለኝ እንደ መሆኔ ምክሬን እነግራችኋለሁ እንጂ። 26 ነገር ግን እንዲህ ይመስለኛል፤ በግድ ይህ ሊመረጥ ይሻላልና እንዲህ ሆኖ ቢኖር ለሰው ይሻለዋል። 27 ከሚስትህ ጋር ሳለህ ከእርስዋ መፋታትን አትሻ፤ ሚስት ከሌለህ ግን ሚስትን አትሻ። 28 ብታገባም ኀጢአት አይሆንብህም፤ ድንግሊቱም ባል ብታገባ ኀጢአት አይሆንባትም፤ ያገቡ ግን ለራሳቸው ድካምን ይሻሉ፤ እኔም ይህን የምላችሁ ስለማዝንላችሁ ነው። 29 ነገር ግን ወንድሞቻችን እንዲህ ይቀናል፤ የዚህ ዓለም ኑሮ ሁሉ ሊያልፍ ቀርቦአልና፤ አሁንም ያገቡ እንዳላገቡ ይሆናሉ። 30 ያለቀሱ እንዳላለቀሱ ይሆናሉ፤ ደስ ያላቸውም ደስ እንዳላላቸው ይሆናሉ፤ የሸጡም እንዳልሸጡ ይሆናሉ፤ የገዙም እንዳልገዙ ይሆናሉ። 31 የበሉ እንዳልበሉ ይሆናሉ፤ የጠጡም እንዳልጠጡ ይሆናሉ፤ የዚህ ዓለም ተድላ ሁሉ ያልፋልና። 32 እኔስ ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ፤ ያላገባ እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኘው የእግዚአብሔርን ነገር ያስባልና። 33 ያገባ ግን ሚስቱን ደስ ሊያሰኝ የዚህን ዓለም ኑሮ ያስባል። 34 እንዲህ ከሆነ ግን ተለያየ፤ አግብታ የፈታች ሴትም ያላገባች ድንግልም ብትሆን ነፍስዋም ሥጋዋም ይቀደስ ዘንድ እግዚአብሔርን ታስበዋለች፤ ያገባች ግን ባልዋን ደስ ልታሰኝ የዚህን ዓለም ኑሮ ታስባለች። 35 ይህንም የምላችሁ እንዲጠቅማችሁ ነው፤ ላጠምዳችሁ ግን አይደለም፤ ኑሮአችሁ አንድ ወገን እንዲሆንና እግዚአብሔርን ያለመጠራጠር እንድታገለግሉት ነው እንጂ። 36 በሸመገለ ጊዜ ስለ ድንግልናው እንደሚያፍር የሚያስብ ሰው ቢኖር እንዲህ ሊሆን ይገባል፤ የወደደውን ያድርግ፤ ቢያገባም ኀጢአት የለበትም። 37 በልቡ የቈረጠና ያላወላወለ ግን የወደደውን ሊያደርግ ይችላል፤ ግድም አይበሉት፤ ድንግልናውንም ይጠብቅ ዘንድ በልቡ ቢጸና መልካም አደረገ። 38 ድንግሊቱን ያገባ መልካም አደረገ፤ ያላገባ ግን የምትሻለውን አደረገ። 39 ሴት ባልዋ በሕይወት ሳለ የታሠረች ናት፤ ባልዋ የሞተ እንደ ሆነ ግን ነጻ ናት፤ የወደደችውን ታግባ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ይሁን። 40 በምክሬ ጸንታ እንዲሁ ብትኖር ግን ብፅዕት ናት፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእኔ ላይ ያለ ይመስለኛል። |