1 ቆሮንቶስ 6 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)በዐመፀኞች ዳኝነት መከራከር ስለማይገባ 1 እንግዲህ በሚነቅፉ ሰዎች ዘንድ ልትከራከሩ አትድፈሩ፤ ከጓደኛው ጋር በዐመፀኞች ዘንድ ሊከራከር የሚችል አለን? በደጋጎች ዘንድ አይደለምን? ከባልንጀራው ጋር ክርክር ያለው ቢኖርም በቅዱሳን ዘንድ ይከራከር፤ በሚነቅፉና በዐመፀኞች ዘንድ ግን አይደለም። 2 ቅዱሳን ሰውን ሁሉ እንደሚዳኙ አታውቁምን? እናንተ ሰውን ሁሉ የምትዳኙ ከሆናችሁ ይህን ትንሹን ነገር ልትዳኙ አይገባችሁምን? 3 የዚህንስ ዓለም ዳኝነት ተዉትና በመላእክት ስንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን? 4 ነገር ግን የዚህ ዓለም ክርክር ያላቸው ሰዎች ቢኖሩ በቤተ ክርስቲያን የተሾሙ የበታች ወንድሞች ይስሙአቸው። 5 ይህንም የምላችሁ ስዘልፋችሁ ነው፤ እንግዲህ ከመካከላቸሁ ወንድማማቾችን ከወንድሞቻቸው ጋር ማስታረቅ የሚችል ሽማግሌ የለምን? 6 ነገር ግን ወንድም ከወንድሙ ጋር ይካሰሳል፤ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋል። 7 እንግዲህ ፀብና ክርክር ካላችሁ፥ ከመጀመሪያው ጀምሮ ውርደት እንደሚሆንባችሁ ዕወቁ፤ እንግዲያማ እንዴት አትነጠቁም? እንዴትስ አትገፉም? 8 አሁንም ቢሆን፥ እናንተ ዐመፀኞችና ቀማኞች ናችሁ፤ እንደዚህም ወንድሞቻችሁን ትበድላላችሁ። መንግሥተ ሰማያትን ስለማይወርሱ ሰዎች 9 ዐመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁምን? አያስቱአችሁ፤ ሴሰኞች፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ፥ ወይም አመንዝራዎች፥ ወይም ቀላጮች፥ ወይም በወንድ ላይ ዝሙትን የሚሠሩ፥ የሚሠሩባቸውም ቢሆኑ፤ 10 ሌቦች፥ ወይም ቀማኞች፥ ወይም ሰካሮች፥ ወይም ተሳዳቢዎች፥ ወይም ነጣቂዎች፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱአትም። 11 እንግዲህ እናንተ እንዲህ ስትሆኑ እነማን ናችሁ? ነገር ግን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፤ ተቀድሳችኋል፤ ጸድቃችኋልም። ሰውነትን ለእግዚአብሔር ክብር ስለ ማድረግ 12 በሆነው ሁሉ ላይ ሥልጣን አለኝ፤ ግን ሁሉ የሚጠቅመኝ አይደለም፤ ሁሉም ይቻለኛል፤ ነገር ግን በእኔ ላይ እንዲሠለጥን የማደርገው ምንም የለም። 13 መብል ለሆድ ነው ፤ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ሁለቱንም ይሽራቸዋል፤ ሥጋችሁም ለእግዚአብሔር ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ እግዚአብሔርም ለሥጋችሁ ነው። 14 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው እግዚአብሔር እኛንም በከሃሊነቱ ያስነሣናል። 15 ሥጋችሁ የክርስቶስ አካል እንደ ሆነ አታውቁምን? እንግዲህ የክርስቶስን አካል ወስዳችሁ የአመንዝራ አካል ታደርጉታላችሁን? አይገባም። 16 ከአመንዝራ ጋር የተገናኘ ከእርስዋ ጋር አንድ አካል እንዲሆን አታውቁምን? መጽሐፍ፥ “ሁለቱ አንድ አካል ይሆናሉ” ብሎአልና። 17 ከእግዚአብሔር ጋር የተዋሐደ ግን ከእርሱ ጋር አንድ መንፈስ ይሆናል። 18 ከዝሙት ራቁ፤ ኀጢአት የሚሠራ ሰው ሁሉ ከሥጋው ውጭ ይሠራልና፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን ራሱ በሥጋው ላይ ኀጢአትን ይሠራል። 19 ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር ለተቀበላችሁት በእናንተ አድሮ ላለ ለመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? ለራሳችሁም አይደላችሁም። 20 በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን በሥጋችሁ አክብሩት። |