1 ቆሮንቶስ 1 - የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ)1 በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ሊሆን ከተጠራ ከጳውሎስና ከወንድማችን ከሶስቴንስ፥ 2 በቆሮንቶስ ሀገር ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለከበሩና ቅዱሳን ለተባሉ የእነርሱና የእኛ ጌታ የሆነውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ስም በየስፍራው ለሚጠሩ ሁሉ፥ 3 ከአባታችን ከእግዚአብሔር፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ሰላምና ጸጋ ለእናንተ ይሁን። 4 ስለ እናንተ በኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ ስለተሰጣችሁ ጸጋ ዘወትር እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። 5 በአነጋገር ሁሉ፥ በዕውቀትም ሁሉ ከብራችሁበታልና። 6 ለክርስቶስ መመስከሬ በእናንተ እንደ ጸና መጠን። 7 ፍጹማንም እንድትሆኑ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስንም መምጣት ተስፋ አድርጋችሁ ፍጹም ጸጋን እንዳታጡ፥ 8 እርሱም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ያለ ነውር ትገኙ ዘንድ እስከ ፍጻሜ ያጸናችኋል። 9 ከልጁ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው። መለያየት እንደማይገባ 10 ወንድሞቻችን! አንድ ቃል እንድትናገሩ፥ እንዳታዝኑ፥ ፍጹማንም እንድትሆኑ፥ ሁላችሁንም፦ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እማልዳችኋለሁ፤ እንዳትለያዩም አንድ ልብና አንድ አሳብ ሆናችሁ ኑሩ። 11 ወንድሞቻችን ሆይ! እንደምትጣሉና እንደምትከራከሩ ከቀሎኤስ ወገኖች ስለ እናንተ ነገሩኝ። 12 እነሆ፥ እርስ በርሳችሁ፥ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ እኔ የአጵሎስ ነኝ፤ እኔ የኬፋ ነኝ፤ እኔ የክርስቶስ ነኝ” የምትሉትን እነግራችኋለሁ። 13 ክርስቶስ ተከፍሎአልን? ወይስ በውኑ ጳውሎስ ስለ እናንተ ተሰቅሎአልን? ወይስ በጳውሎስ ስም ተጠምቃችኋልን? 14 ከቀርስጶስና ከጋይዮስ በቀር ከእናንተ ወገን ሌላ ስላላጠመቅሁ እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ። 15 በእርሱ ስም ተጠመቅን የሚል እንዳይኖር። 16 ነገር ግን የእስጢፋኖስን ቤተ ሰብእ አጥምቄአለሁ፤ እንግዲህ ሌላም ያጠመቅሁት እንዳለ አላውቅም። ስለ መስቀል 17 ክርስቶስ ወንጌልን ለመስበክ እንጂ ለማጥመቅ አልላከኝምና፥ የክርስቶስን መስቀሉን ከንቱ እንዳናደርግ ነገርን በማራቀቅ አይደለም። 18 የመስቀሉ ነገር በሚጠፉ ሰዎች ዘንድ ስንፍና ነውና፥ ለምንድነው ለእኛ ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው። 19 መጽሐፍ እንዲህ ብሎአልና፥ “እኔ የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ፤ የመካሪዎችንም ምክር እንቃለሁ።” 20 እንግዲህ ጥበበኛ ማን ነው? ጸሓፊስ ማን ነው? ይህን ዓለምስ የሚመረምረው ማን ነው? እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ጥበብ ስንፍና አላደረገውምን? 21 ሰዎች በጥበባቸው በማያውቁት በእግዚአብሔር ጥበብ ስንፍና በሚመስላቸው ትምህርት ያመኑትን ሊያድናቸው እግዚአብሔር ወድዶአልና። 22 አይሁድ ምልክትን ይጠይቃሉ፤ የጽርዕ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ። 23 እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ስንፍና ነው። 24 ለእኛ ለዳንነው ግን ከአይሁድ፥ ከአረሚም ብንሆን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ኀይል ነው፤ የእግዚአብሔርም ጥበብ ነው። 25 የእግዚአብሔር ስንፍና ከሰው ይልቅ ይጠበባልና፥ የእግዚአብሔርም ድካም ከሰው ይልቅ ይበረታልና። 26 ወንድሞቻችን! እንግዲህ እንዴት እንደ ተጠራችሁ እዩ፤ በሥጋ እጅግ ብዙዎች ዐዋቂዎች አይደላችሁምና፥ ብዙዎች ኀያላንም አይደላችሁምና፥ በዘመድም ብዙዎች ደጋጎች አይደላችሁምና። 27 ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን ሊያሳፍር የዚህን ዓለም ሰነፎች መረጠ፤ ኀይለኞችንም ያሳፍር ዘንድ እግዚአብሔር የዚህን ዓለም ደካሞች መረጠ። 28 አለን የሚሉትንም ያሳፍር ዘንድ ዘመድ የሌላቸውንና የተናቁትን፥ ከቍጥርም ያልገቡትን እግዚአብሔር መረጠ። 29 ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። 30 እናንተም በኢየሱስ ክርስቶስ ከእርሱ ናችሁ፤ በእርሱም ከእግዚአብሔር ጥበብንና ጽድቅን፥ ቅድስናንና ቤዛነትን አገኘን። 31 መጽሐፍ እንደ አለው ይሆን ዘንድ “የሚመካስ በእግዚአብሔር ይመካ።” |