ማሕልየ መሓልይ 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ምነው አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ፣ እንደ ወንድሜ በሆንህ! ከዚያም ውጭ ባገኝህ፣ እስምህ ነበር፤ ታዲያ ማንም ባልናቀኝ! 2 እኔም ወደ አስተማረችኝ፣ ወደ እናቴም ቤት፣ እጅህን ይዤ በወሰድሁህ ነበር፤ የምትጠጣውን ጣፋጭ የወይን ጠጅ፣ የሮማኔን ጭማቂም በሰጠሁህ። 3 ግራ እጁን ተንተርሻለሁ፤ ቀኝ እጁም ዐቅፎኛል። 4 እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት፤ ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት አማፅናችኋለሁ። ባልንጀሮቿ 5 ውዷን ተደግፋ፣ ከምድረ በዳ የምትወጣ ይህች ማን ናት? ከእንኮይ ዛፍ ሥር አስነሣሁህ፤ በዚያ እናትህ ፀነሰችህ፤ በዚያም ታምጥ የነበረችው አንተን ወለደችህ። ሙሽራዪቱ 6 በልብህ እንዳለ፣ በክንድህም እንደምትይዘው ማኅተም አስቀምጠኝ፤ ፍቅር እንደ ሞት የበረታች፣ ቅናቷም እንደ መቃብር ጨካኝ ናትና፤ እንደሚንቦገቦግ እሳት፣ እንደ ኀይለኛም ነበልባል ትነድዳለች። 7 የውሃ ብዛት ፍቅርን ሊያጠፋ አይችልም፤ ፈሳሾችም አያሰጥሟትም፤ ሰው የቤቱን ሀብት ሁሉ ስለ ፍቅር ቢሰጥ ፈጽሞ ይናቃል። ባልንጀሮቿ 8 ትንሽ እኅት አለችን፤ ጡትም ገና አላወጣችም፤ ስለ እርሷ በምንጠየቅበት ቀን ምን ማድረግ እንችል ይሆን? 9 እርሷ ቅጥር ብትሆን፣ በላይዋ የብር መጠበቂያ ማማ እንሠራባታለን፤ በር ብትሆን፣ በዝግባ ዕንጨት እንከልላታለን። ሙሽራዪቱ 10 እነሆ እኔ ቅጥር ነኝ፤ ጡቶቼም እንደ ማማ ግንቦች ናቸው፤ እኔም በዐይኖቹ ፊት፣ ሰላምን እንደሚያመጣ ሰው ሆንሁ። 11 ሰሎሞን በብኤላሞን የወይን ተክል ቦታ ነበረው፤ የወይኑን ተክል ቦታም ለአትክልተኞች አከራየው፤ እያንዳንዳቸውም የፍሬውን ዋጋ፣ አንድ አንድ ሺሕ ሰቅል ብር ያመጡለት ነበር። 12 የወይኔ ተክል ቦታ የራሴ፣ የግሌ ነው፤ ሰሎሞን ሆይ፤ አንድ ሺሑ ሰቅል ለአንተ፤ ፍሬውን ለሚጠብቁ ደግም ሁለት መቶ ይሁን። ሙሽራው 13 አንቺ በአትክልቱ ቦታ የምትኖሪ ሆይ፤ ባልንጀሮቼ ድምፅሽን ይሰማሉ፤ እስኪ እኔም ልስማው። ሙሽራዪቱ 14 ውዴ ሆይ፤ ቶሎ ናልኝ፤ ሚዳቋን፣ ወይም በቅመም ተራራ ላይ የሚዘልል፣ የዋሊያን ግልገል ምሰል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.