መዝሙር 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምመዝሙር 21 ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር። 1 እግዚአብሔር ሆይ፤ ንጉሥ በኀይልህ ደስ ይለዋል፤ በምትሰጠውም ድል እጅግ ሐሤት ያደርጋል። 2 የልቡን መሻት ሰጠኸው፤ የከንፈሮቹንም ልመና አልከለከልኸውም። ሴላ 3 መልካም በረከት ይዘህ በመንገዱ ላይ ጠብቀኸው፤ የንጹሕ ወርቅ ዘውድም በራሱ ላይ ደፋህለት። 4 ሕይወትን ለመነህ፤ ረዥም ዘመናትንም እስከ ዘላለም ሰጠኸው። 5 በአቀዳጀኸው ድል ክብሩ ታላቅ ሆነ፤ ክብርንና ግርማን አጐናጸፍኸው። 6 ዘላለማዊ በረከትን ሰጠኸው፤ ከአንተ ዘንድ በሚገኝ ፍሥሓም ደስ አሠኘኸው፤ 7 ንጉሡ በእግዚአብሔር ተማምኗልና፤ ከልዑልም ጽኑ ፍቅር የተነሣ፣ ከቆመበት አይናወጥም። 8 እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ ታገኛቸዋለች፤ ቀኝ እጅህም የሚጠሉህን ፈልጋ ትይዛለች። 9 በምትገለጥበት ጊዜ፣ እሳት እንደሚንቀለቀልበት ምድጃ ታደርጋቸዋለህ፤ እግዚአብሔር በመዓቱ እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል፤ እሳቱም ሙጥጥ አድርጋ ትበላቸዋለች። 10 ዘራቸውን ከምድር፣ ዘር ማንዘራቸውንም ከሰው ልጆች መካከል ታጠፋለህ። 11 ክፋት ቢያስቡብህ፣ ተንኰል ቢወጥኑብህም አይሳካላቸውም፤ 12 በመጡበት ትመልሳቸዋለህና፤ ቀስትህንም በፊታቸው ላይ ታነጣጥራለህ። 13 እግዚአብሔር ሆይ፤ በብርታትህ ከፍ ከፍ በል፤ ኀይልህን እናወድሳለን፤ እንዘምራለንም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.