Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘኍል 23 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የመጀመሪያው የበለዓም ንግር

1 በለዓም፣ “እዚህ ሰባት መሠዊያ ሥራልኝ፤ ሰባት ኰርማዎችና ሰባት አውራ በጎችም አዘጋጅልኝ” አለው።

2 ባላቅም በለዓም እንደ ነገረው አደረገ፤ ሁለቱም በእያንዳንዱ መሠዊያ ላይ አንድ ኰርማና አንድ አውራ በግ አቀረቡ።

3 ከዚያም በለዓም ባላቅን፣ “እኔ ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ፤ ምናልባትም እግዚአብሔር ሊገናኘኝ ይመጣ ይሆናል፤ የሚገልጥልኝንም ሁሉ እነግርሃለሁ” አለው። ከዚያም በለዓም ወደ አንድ ገላጣ ኰረብታ ሄደ።

4 እግዚአብሔር ተገናኘው፤ በለዓምም፣ “እነሆ፤ ሰባት መሠዊያዎች አዘጋጅቻለሁ፤ በእያንዳንዱም ላይ አንድ ኰርማና አንድ አውራ በግ አቅርቤአለሁ” አለው።

5 እግዚአብሔርም በበለዓም አፍ መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመልሰህ ይህን መልእክት ንገረው” አለው።

6 እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅን ከመላው የሞዓብ አለቆች ጋራ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አገኘው።

7 ከዚያም በለዓም ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤ “ባላቅ ከአራም አመጣኝ፣ የሞዓብ ንጉሥ ከምሥራቅ ተራሮች። ‘ና ያዕቆብን ርገምልኝ፤ መጥተህም እስራኤልን አውግዝልኝ’ አለኝ።

8 እግዚአብሔር ያልረገመውን፣ እኔ እንዴት ረግማለሁ? እግዚአብሔር ያላወገዘውንስ፣ እንዴት አወግዛለሁ?

9 ከዐለታማ ተራሮች ጫፍ ሆኜ አየዋለሁ፤ በከፍታዎቹም ላይ ሆኜ እመለከተዋለሁ፤ ተለይቶ የሚኖረውን፣ ራሱንም ከሌሎች ሕዝቦች ጋራ የማይቈጥረውን ሕዝብ አያለሁ።

10 የያዕቆብን ትቢያ ማን ቈጥሮ ይዘልቃል? የእስራኤልንስ ሩብ ማን ይቈጥረዋል። የጻድቁን ሞት እኔ ልሙት፤ ፍጻሜዬም የርሱ ዐይነት ፍጻሜ ትሁን!”

11 ባላቅም በለዓምን፣ “እንዴት እንዲህ ታደርገኛለህ? ጠላቶቼን እንድትረግምልኝ አመጣሁህ፤ አንተ ግን ባረክሃቸው እንጂ ምንም አላደረግህልኝም!” አለው።

12 እርሱም መልሶ “እግዚአብሔር በአፌ ያስቀመጠውን መናገር አይገባኝምን?” አለው።


ሁለተኛው የበለዓም ንግር

13 ከዚህ በኋላ ባላቅ፣ “እነርሱን ማየት ወደምትችልበት ወደ ሌላ ቦታ እንሂድ፤ በእዚያም ሁሉን ሳይሆን በከፊል ብቻ ታያቸዋለህ፤ እዚያም ሆነህ እነርሱን ርገምልኝ” አለው።

14 ስለዚህም በፈስጋ ተራራ ጫፍ ላይ ወዳለው ወደ ጾፊም ሜዳ ወሰደው፤ እዚያም ሰባት መሠዊያ ሠርቶ በእያንዳንዱ ላይ አንድ ኰርማና አንድ አውራ በግ ሠዋ።

15 በለዓምም ባላቅን፣ “እርሱን ለመገናኘት ወደዚያ ስሄድ፣ አንተ እዚሁ መሥዋዕትህ አጠገብ ቈይ” አለው።

16 እግዚአብሔር በለዓምን ተገናኘው፤ በአፉም መልእክት አስቀምጦ፣ “ወደ ባላቅ ተመለስና ይህን መልእክት ንገረው” አለው።

17 እርሱም ተመልሶ ሲሄድ ባላቅን ከመላው የሞዓብ አለቆች ጋራ በመሠዊያው አጠገብ ቆሞ አገኘው፤ ባላቅም፣ “እግዚአብሔር ምን አለ?” ሲል ጠየቀው።

18 ከዚያም ንግሩን እንዲህ ሲል ጀመረ፤ “ባላቅ ሆይ ተነሣ፤ ስማኝ፤ የሴፎር ልጅ ሆይ አድምጠኝ፤

19 ይዋሽ ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፤ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም፤ ተናግሮ አያደርገውምን? ተስፋ ሰጥቶስ አይፈጽመውምን?

20 እባርክ ዘንድ ትእዛዝ ተቀብያለሁ፤ እርሱ ባርኳል፤ እኔም ልለውጠው አልችልም።

21 “በያዕቆብ መጥፎ ነገር አልተገኘም፤ በእስራኤልም ጕስቍልና አልታየም፤ እግዚአብሔር አምላኩ ከርሱ ጋራ ነው፤ የንጉሡም እልልታ በመካከላቸው ነው።

22 እግዚአብሔር ከግብጽ አወጣቸው፤ ብርታታቸውም እንደ ጐሽ ብርታት ነው።

23 በያዕቆብ ላይ የሚሠራ አስማት የለም፤ በእስራኤልም ላይ የሚሠራ ሟርት አይኖርም፤ ለያዕቆብና ለእስራኤል፣ ‘እግዚአብሔር ያደረገውን እዩ!’ ይባልላቸዋል።

24 ሕዝቡ እንደ እንስት አንበሳ ይነሣል፤ ያደነውን እስኪያነክት፣ የገደለውንም ደም እስኪጠጣ፣ እንደማያርፍ አንበሳ ሆኖ ይነሣል።”

25 በዚህ ጊዜ ባላቅ በለዓምን፣ “እንግዲያውስ ፈጽሞ አትርገማቸው፤ ፈጽሞም አትመርቃቸው!” አለው።

26 በለዓምም፣ “እግዚአብሔር የሚለኝን ሁሉ ማድረግ እንዳለብኝ አልነገርሁህምን?” ሲል መለሰለት።


ሦስተኛው የበለዓም ንግር

27 ከዚህ በኋላ ባላቅ በለዓምን፣ “በል እንግዲያው ወደ ሌላ ቦታ ልውሰድህ፤ ከዚያ ሆነህ እንድትረግምልኝ ምናልባት እግዚአብሔር ይፈቅድልህ ይሆናል” አለው።

28 ባላቅም በለዓምን ምድረ በዳው ቍልቍል ወደሚታይበት ወደ ፌጎር ጫፍ አወጣው።

29 በለዓምም፣ “ሰባት መሠዊያዎች እዚህ ሥራልኝ፤ ሰባት ኰርማዎችና ሰባት አውራ በጎችም አዘጋጅልኝ” አለው።

30 ባላቅም በለዓም እንደ ነገረው አደረገ፤ በእያንዳንዱም መሠዊያ ላይ አንድ ኰርማና አንድ አውራ በግ ሠዋ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች