ዘኍል 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየየነገዱ አሰፋፈር 1 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤ 2 “እስራኤላውያን ከምስክሩ ድንኳን ትይዩ ዙሪያውን ጥቂት ራቅ ብለው እያንዳንዱ ሰው በየዐርማውና በየቤተ ሰቡ ምልክት ሥር ይስፈር።” 3 በምሥራቅ በኩል በፀሓይ መውጫ፤ የይሁዳ ምድብ፤ በየሰራዊቱና በዐርማቸው ሥር ይስፈር፤ የይሁዳ ሕዝብ አለቃ የአሚናዳብ ልጅ ነአሶን ነው፤ 4 የሰራዊቱም ብዛት ሰባ አራት ሺሕ ስድስት መቶ ነው። 5 ከእነዚህ ቀጥሎ የይሳኮር ነገድ ይሰፍራል፤ የይሳኮር ሕዝብ አለቃ የሶገር ልጅ ናትናኤል ሲሆን፣ 6 የሰራዊቱም ብዛት ዐምሳ አራት ሺሕ አራት መቶ ነው። 7 ከዚያም የዛብሎን ነገድ ይቀጥላል፤ የዛብሎን ሕዝብ አለቃ የኬሎን ልጅ ኤልያብ ሲሆን፣ 8 የሰራዊቱም ብዛት ዐምሳ ሰባት ሺሕ አራት መቶ ነው። 9 በየሰራዊታቸው ሆነው ከአይሁድ ምድብ የተመዘገቡ አንድ መቶ ሰማንያ ስድስት ሺሕ አራት መቶ ናቸው፤ እነዚህ አስቀድመው ይወጣሉ። 10 በደቡብ በኩል፤ የሮቤል ምድብ ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ይሆናል፤ የሮቤል ሕዝብ አለቃ የስዲዮር ልጅ ኤሊሱር ሲሆን፣ 11 የሰራዊቱም ብዛት አርባ ስድስት ሺሕ ዐምስት መቶ ነው። 12 ከእነዚህ ቀጥሎ የስምዖን ነገድ ይሰፍራል፤ የስምዖን ሕዝብ አለቃ የሱሪሰዳይ ልጅ ሰለሚኤል ሲሆን፣ 13 የሰራዊቱም ብዛት ዐምሳ ዘጠኝ ሺሕ ሦስት መቶ ነው። 14 ከዚያም የጋድ ነገድ ይቀጥላል፤ የጋድ ሕዝብ አለቃ የራጉኤል ልጅ ኤሊሳፍ ሲሆን፣ 15 የሰራዊቱም ብዛት አርባ ዐምስት ሺሕ ስድስት መቶ ዐምሳ ነው። 16 በየሰራዊታቸው ሆነው ከሮቤል ምድብ የተመዘገቡት ወንዶች በሙሉ አንድ መቶ ዐምሳ አንድ ሺሕ አራት መቶ ዐምሳ ናቸው፤ እነዚህ ቀጥለው ይመጣሉ። 17 ከዚህ በኋላ የመገናኛው ድንኳንና የሌዋውያን ምድብ በመካከል ሆነው ይጓዛሉ፤ እያንዳንዳቸውም አሰፋፈራቸውን በመከተል ቦታቸውን ጠብቀው በዐርማቸው ሥር ይጓዛሉ። 18 በምዕራብ በኩል፤ የኤፍሬም ምድብ ሰራዊት በዐርማቸው ሥር ይሆናል፤ የኤፍሬም ሕዝብ አለቃ የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሳማ ሲሆን፣ 19 የሰራዊቱም ብዛት አርባ ሺሕ ዐምስት መቶ ነው። 20 ከእነዚህም የምናሴ ነገድ ይቀጥላል፣ የምናሴ ሕዝብ አለቃ የፍዳሱር ልጅ ገማልኤል ሲሆን፣ 21 የሰራዊቱም ብዛት ሠላሳ ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ነው። 22 ከዚያም የብንያም ነገድ ይቀጥላል፣ የብንያም ሕዝብ አለቃ የጋዴዮን ልጅ አቢዳን ሲሆን፣ 23 የሰራዊቱም ብዛት ሠላሳ ዐምስት ሺሕ አራት መቶ ነው። 24 በየሰራዊታቸው ሆነው ከኤፍሬም ምድብ የተመዘገቡት ወንዶች በሙሉ አንድ መቶ ስምንት ሺሕ አንድ መቶ ናቸው፤ እነዚህ ሦስተኛ ሆነው ይመጣሉ። 25 በሰሜን በኩል፤ የዳን ምድብ ሰራዊት በዐርማው ሥር ይሆናል፤ የዳን ሕዝብ አለቃ የአሚሳዳይ ልጅ አኪዔዘር ሲሆን፣ 26 የሰራዊቱም ብዛት ስድሳ ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ ነው። 27 የአሴር ነገድ ከእነዚህ ቀጥሎ ይሰፍራል፤ የአሴር ሕዝብ አለቃ የኤክራን ልጅ ፋግኤል ሲሆን፣ 28 የሰራዊቱም ብዛት አርባ አንድ ሺሕ ዐምስት መቶ ነው። 29 ከዚያም የንፍታሌም ነገድ ይቀጥላል፤ የንፍታሌም ሕዝብ አለቃ የዔናን ልጅ አኪሬ ሲሆን፣ 30 የሰራዊቱም ብዛት ዐምሳ ሦስት ሺሕ አራት መቶ ነው። 31 በየሰራዊታቸው ሆነው ከዳን ምድብ የተመዘገቡት ወንዶች ሁሉ አንድ መቶ ዐምሳ ሰባት ሺሕ ስድስት መቶ ናቸው፤ እነርሱም በዐርማቸው ሥር በመጨረሻ ይመጣሉ። 32 በየቤተ ሰባቸው፣ በየምድባቸውና በየሰራዊታቸው የተመዘገቡት እስራኤላውያን ስድስት መቶ ሦስት ሺሕ ዐምስት መቶ ዐምሳ ናቸው፤ 33 ያም ሆኖ ግን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሌዋውያኑ ከሌሎቹ እስራኤላውያን ጋራ አልተቈጠሩም። 34 ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ በየዐርማውም ሥር የሰፈሩትና፣ እያንዳንዳቸው በየጐሣቸውና በየቤተ ሰባቸው የተጓዙት በዚህ ሁኔታ ነበር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.