ዘኍል 15 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምተጨማሪ ቍርባን 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እንድትኖሩበት ወደምሰጣችሁ ምድር ከገባችሁ በኋላ፣ 3 ስእለታችሁን ለመፈጸም ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ለማድረግ ወይም በበዓላታችሁ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ከላም ወይም ከበግ መንጋ በእሳት ለእግዚአብሔር ስታቀርቡ 4 መሥዋዕቱን ይዞ የሚመጣው ሰው በሂን አንድ አራተኛ ዘይት የተለወሰ የኢፍ አንድ ዐሥረኛ የላመ ዱቄት የእህል ቍርባን ለእግዚአብሔር ያቀርባል። 5 ለሚቃጠል ወይም ለዕርድ መሥዋዕት ከሚቀርብ ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋራ የሂን አንድ አራተኛ የወይን ጠጅ የመጠጥ ቍርባን ዐብራችሁ አዘጋጁ። 6 “ ‘ከአውራ በግ ጋራ በሂን ሢሶ ዘይት የተለወሰ የኢፍ ሁለት ዐሥረኛ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን አዘጋጁ፤ 7 እንዲሁም ለመጠጥ ቍርባን የሚሆን የሂን አንድ ሦስተኛ የወይን ጠጅ አዘጋጁ፤ ይህንም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሽታ ያለው አድርጋችሁ አቅርቡ። 8 “ ‘አንዱን ወይፈን ለተለየ ስእለት ወይም ለኅብረት የሚቀርብ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም የዕርድ መሥዋዕት አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር በምታዘጋጁበት ጊዜ፣ 9 ከወይፈኑ ጋራ በግማሽ ሂን ዘይት የተለወሰ የኢፍ ሦስት ዐሥረኛ የላመ ዱቄት ቍርባን ዐብራችሁ አምጡ። 10 እንዲሁም ለመጠጥ ቍርባን የሚሆን ግማሽ ሂን የወይን ጠጅ አቅርቡ፤ ይህም በእሳት የሚቀርብና ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ይሆናል። 11 እያንዳንዱ ወይፈን ወይም አውራ በግ፣ እያንዳንዱ የበግም ሆነ የፍየል ጠቦት በዚህ ሁኔታ ይዘጋጅ። 12 ባዘጋጃችሁት ቍጥር ልክ ይህን ለእያንዳንዱ አድርጉ። 13 “ ‘ማንኛውም የአገር ተወላጅ የሆነ በእሳት የሚቀርብ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች በዚሁ ሁኔታ ያድርግ። 14 ለሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ መጻተኛ ወይም በመካከላችሁ የሚኖር ማንኛውም ሰው በእሳት የሚቀርብ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ ልክ እናንተ እንደምታደርጉት ያድርግ። 15 ማኅበረ ሰቡ ለእናንተም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ አንድ ዐይነት ደንብ ይኖረዋል፤ ይህም በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ የማይሻር ሥርዐት ነው። እናንተም ሆናችሁ መጻተኞቹ በእግዚአብሔር ፊት እኩል ትታያላችሁ፤ 16 ለእናንተም ሆነ በመካከላችሁ ለሚኖር መጻተኛ ይኸው ሕግና ሥርዐት እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል።’ ” 17 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 18 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እኔ ወደምወስዳችሁ ምድር ገብታችሁ፣ 19 የምድሪቱን በረከት ስትመገቡ ከዚሁ ላይ አንሥታችሁ ለእግዚአብሔር ቍርባን አቅርቡ። 20 ይህንም ከመጀመሪያው ዱቄት ላይ ኅብስት ጋግራችሁ ከዐውድማ እንደ ተገኘ ቍርባን አድርጋችሁ አምጡ። 21 በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ከመጀመሪያው ዱቄት ላይ አንሥታችሁ ይህን ቍርባን ለእግዚአብሔር ትሰጣላችሁ። ባለማወቅ ስለሚደረግ ኀጢአት የሚቀርብ መሥዋዕት 22 “ ‘እንግዲህ ካለማወቅ የተነሣ እግዚአብሔር ለሙሴ ከሰጣቸው ትእዛዞች አንዱን ሳትፈጽሙ ብትቀሩ፣ ይህም ማለት 23 እግዚአብሔር ትእዛዞቹን ከሰጠበት ዕለት ጀምሮ በተከታታይ ትውልዶች በሙሴ አማካይነት ያዘዛችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ ባታደርጉ፣ 24 ይህም የተፈጸመው ሆነ ተብሎ ሳይሆንና ማኅበረ ሰቡም ሳያውቀው ከሆነ፣ ማኅበረ ሰቡ በሙሉ ሽታው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አድርጎ አንድ ወይፈን በእሳት ለሚቃጠል መሥዋዕት ያቅርብ፤ ከዚሁም ጋራ ሥርዐቱ የሚጠይቀውን የእህል ቍርባንና የመጠጥ ቍርባን ደግሞም ለኀጢአት መሥዋዕት ተባዕት ፍየል ያቅርብ። 25 ካህኑም ለመላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ያስተሰርያል፤ እነርሱም ይቅር ይባላሉ፤ ምክንያቱም ባለማወቅ የተፈጸመ ስለ ሆነና ስለ ስሕተታቸውም በእሳት የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስላቀረቡ ነው። 26 ባለማወቅ የተደረገውን ስሕተት ሁሉም የፈጸሙት ስለ ሆነ፣ መላው የእስራኤል ማኅበረ ሰብና በመካከላቸው የሚኖር መጻተኛ ሁሉ ይቅር ይባላል። 27 “ ‘ነገር ግን አንድ ሰው ካለማወቅ የተነሣ በግሉ ኀጢአት ቢሠራ ግን ለኀጢአት መሥዋዕት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያምጣ። 28 ከዚያም ካህኑ፣ ባለማወቅ ኀጢአት ሠርቶ ለተሳሳተው ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፤ ስርየት በሚደረግለትም ጊዜ ሰውየው ይቅር ይባላል። 29 ያገር ተወላጅ እስራኤላዊ ይሁን ወይም መጻተኛ ባለማወቅ ኀጢአት ከሠራ በማናቸውም ሰው ላይ ሕጉ እኩል ተፈጻሚነት ይኖረዋል። 30 “ ‘ያገር ተወላጅም ይሁን መጻተኛ ሆነ ብሎ ኀጢአት የሚሠራ ማንኛውም ሰው ግን እግዚአብሔርን ስለሚያቃልል ያ ሰው ከወገኖቹ ተለይቶ ይጥፋ። 31 የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ናቀ፣ ትእዛዞቹንም ስለ ጣሰ ያ ሰው በርግጥ ተለይቶ መጥፋት አለበት፤ ጥፋቱ የራሱ ነው።’ ” ሰንበትን የሻረው በሞት ተቀጣ 32 እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ አንድ ሰው በሰንበት ቀን ዕንጨት ሲለቅም ተገኘ። 33 ዕንጨት ሲለቅም ያገኙትም ሰዎች ሰውየውን ወደ ሙሴ፣ ወደ አሮንና ወደ መላው የእስራኤል ማኅበር አመጡት፤ 34 በሰውየው ላይ ምን መደረግ እንዳለበት ግልጽ የሆነ ነገር ባለመኖሩ በጥበቃ ሥር እንዲቈይ አደረጉት። 35 ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ሰውየው ይሙት፤ መላውም ማኅበር ከሰፈር ውጭ በድንጋይ ይውገረው” አለው፤ 36 ስለዚህ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ማኅበሩ ሰውየውን ከሰፈር አውጥቶ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ወገረው። ስለ ልብስ ዘርፍ የተሰጠ መመሪያ 37 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 38 “እስራኤላውያንን ተናገራቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ በየልብሳችሁ ጫፍ ላይ ዘርፍ አድርጉ፤ እያንዳንዱም ዘርፍ ሰማያዊ ጥለት ይኑረው። 39 ልባችሁ የተመኘውን፣ ዐይናችሁ ያየውን ሁሉ ተከትላችሁ እንዳታመነዝሩ እነዚህን ዘርፎች በማየት የእግዚአብሔርን ትእዛዞች በማስታወስ እንድትታዘዙ ማስታወሻ ይሆኗችኋል። 40 ስለዚህ ትእዛዞቼን ሁሉ ለመፈጸም ታስባላችሁ፤ ለአምላካችሁም የተቀደሳችሁ ትሆናላችሁ። 41 አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።’ ” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.