ሚልክያስ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየ እግዚአብሔር ቀን 1 “እነሆ፤ እንደ ምድጃ እሳት የሚነድድ ቀን ይመጣል፤ ትዕቢተኞች ሁሉና ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ገለባ ይሆናሉ፤ ያ የሚመጣው ቀንም ያቃጥላቸዋል” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። “ሥርም ሆነ ቅርንጫፍ አያስቀርላቸውም። 2 ስሜን ለምትፈሩ ለእናንተ ግን የጽድቅ ፀሓይ በክንፎቿ ፈውስ ይዛ ትወጣለች፤ እናንተም እንደ ሠባ እንቦሳ እየቦረቃችሁ ትወጣላችሁ። 3 እኔ በምሠራበት ቀን ክፉዎችን ትረግጣላችሁ፤ ከእግራችሁ ጫማ በታች ዐመድ ይሆናሉ” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 4 “ለእስራኤል ሁሉ ሕጎችና ሥርዐቶች ይሆኑ ዘንድ፣ ለአገልጋዬ ለሙሴ በኮሬብ የሰጠሁትን ሕግ አስቡ። 5 “እነሆ፤ ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ። 6 መጥቼ ምድርን በርግማን እንዳላጠፋ፣ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.