ሆሴዕ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 “ወንድሞቻችሁን ‘ሕዝቤ’፣ እኅቶቻችሁንም ‘ተወዳጆቼ’ ብላችሁ ጥሯቸው። የእስራኤል መቀጣትና መመለስ 2 “እናታችሁን ምከሯት፤ ምከሯት፤ እርሷ ሚስቴ አይደለችም፤ እኔም ባሏ አይደለሁምና። ከፊቷ የዘማዊነት አስተያየትን፣ ከጡቶቿም መካከል ምንዝርናዋን ታስወግድ። 3 አለዚያ ገፍፌ ዕርቃኗን አስቀራታለሁ፤ እንደ ተወለደችበትም ቀን አደርጋታለሁ፤ እንደ ምድረ በዳ፣ እንደ ደረቅም ምድር አደርጋታለሁ፤ በውሃ ጥምም እገድላታለሁ። 4 ለልጆቿ አልራራላቸውም፤ የምንዝርና ልጆች ናቸውና። 5 እናታቸው አመንዝራ ናት፤ በውርደትም ፀንሳቸዋለች፤ እርሷም፣ ‘እንጀራዬንና ውሃዬን ይሰጡኛል፤ ሱፌንና የሐር ልብሴን፣ ዘይቴንና መጠጤን ይሰጡኛል፤ ስለዚህ ውሽሞቼን ተከትዬ እሄዳለሁ’ አለች። 6 በዚህ ምክንያት መንገዷን በእሾኽ እዘጋለሁ፤ መውጫ መንገድ እንዳታገኝም ዙሪያዋን በግንብ ዐጥራለሁ። 7 ውሽሞቿን ተከትላ ትሄዳለች፤ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸዋለች፤ ሆኖም አታገኛቸውም። ከዚያም እንዲህ ትላለች፤ ‘ወደ ቀድሞ ባሌ እመለሳለሁ፤ የፊተኛው ኑሮዬ ከአሁኑ ይሻለኛልና።’ 8 እርሷም እህል፣ ዘይትና አዲስ የወይን ጠጅ የሰጠኋት፣ ለበኣል አምልኮ ያደረጉትን፣ ብርንና ወርቅን ያበዛሁላት፣ እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም። 9 “ስለዚህ እህሌን በመከር ጊዜ፣ አዲሱም የወይን ጠጅ በደረሰ ጊዜ እወስዳለሁ፤ ዕርቃኗንም እንዳትሸፍንበት፣ ሱፍና የሐር ልብሴን መልሼ እወስድባታለሁ። 10 አሁንም በውሽሞቿ ፊት፣ ነውሯን እገልጣለሁ፤ ከእጄም የሚያድናት የለም። 11 የደስታ በዓሎቿን ሁሉ፣ የዓመት በዓላቷንና የወር መባቻዎቿን፣ ሰንበቶቿንና የተመረጡ በዓላቷን ሁሉ አስቀራለሁ። 12 ከውሽሞቼ የተቀበልሁት ዋጋ ነው የምትለውን የወይን ተክሎቿንና የበለስ ዛፎቿን አጠፋለሁ፤ ጫካ አደርገዋለሁ፤ የዱር አራዊትም ይበሉታል። 13 ለበኣል አማልክት ዕጣን ስላጠነችባቸው ቀናት እቀጣታለሁ፤ በጌጣጌጥና በቀለበቶች ራሷን አስጊጣለች፤ ውሽሞቿንም ተከትላ ሄዳለች፤ እኔን ግን ረስታለች” ይላል እግዚአብሔር። 14 “ስለዚህ እነሆ፤ አባብላታለሁ፤ ወደ ምድረ በዳም እወስዳታለሁ፤ በፍቅር ቃል አነጋግራታለሁ። 15 በዚያም የወይን ተክሏን እመልስላታለሁ፤ የአኮርንም ሸለቆ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ። በዚያም ከግብጽ እንደ ወጣችበት ቀን፣ እንደ ልጅነቷም ጊዜ ትዘምራለች። 16 “በዚያ ቀን፣ ‘ባሌ’ ብለሽ፣ ትጠሪኛለሽ” ይላል እግዚአብሔር። “ከእንግዲህም፣ ‘ጌታዬ’ ብለሽ አትጠሪኝም። 17 የበኣል አማልክትን ስም ከአንደበቷ አስወግዳለሁ፤ ከእንግዲህም ስሞቻቸው አይነሡም። 18 በዚያ ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፣ በምድርም ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ጋራ፣ ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ሁሉም ያለ ሥጋት እንዲኖሩ፣ ቀስትን፣ ሰይፍንና ጦርነትን፣ ከምድሪቱ አስወግዳለሁ። 19 ለእኔ እንድትሆኚ ለዘላለም ዐጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍትሕ፣ በፍቅርና በርኅራኄም ዐጭሻለሁ። 20 በታማኝነት ዐጭሻለሁ፤ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂያለሽ።” 21 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ቀን እኔ እመልሳለሁ፤ ለሰማያት እመልሳለሁ፤ እነርሱም ለምድር ምላሽ ይሰጣሉ፤ 22 ምድርም ለእህል፣ ለአዲስ የወይን ጠጅና ለዘይት ምላሽ ትሰጣለች፤ እነርሱም ለኢይዝራኤል ምላሽ ይሰጣሉ። 23 ስለ ራሴ ስል በምድሪቱ እተክላታለሁ፤ ‘ምሕረትን ያላገኘ’ ብዬ የጠራሁትንም እምረዋለሁ፤ ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ ተብለው የተጠሩትንም፣ ‘ሕዝቤ’ እላቸዋለሁ፤ እነርሱም፣ ‘አንተ አምላኬ ነህ’ ይላሉ።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.