ሆሴዕ 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 እስራኤል የተንዠረገገ ወይን ነበር፤ ብዙ ፍሬም አፈራ፤ ፍሬው በበዛ መጠን፣ ብዙ መሠዊያዎችን ሠራ፤ ምድሩ በበለጸገ መጠን፣ የጣዖታት ማምለኪያ ዐምዶችን አስጌጠ። 2 ልባቸው አታላይ ነው፤ ስለዚህም በደላቸውን ይሸከማሉ። እግዚአብሔር መሠዊያዎቻቸውን ያወድማል፤ የጣዖት ማምለኪያ ዐምዶቻቸውን ያፈራርሳል። 3 እነርሱም፣ “እኛ ንጉሥ የለንም፤ እግዚአብሔርን አላከበርንምና፤ ንጉሥ ቢኖረንስ፣ ምን ሊያደርግልን ይችል ነበር?” ይላሉ። 4 ከንቱ ተስፋ ይሰጣሉ፤ በሐሰት በመማል፣ ቃል ኪዳን ያደርጋሉ፤ ስለዚህም ፍርድ፣ በዕርሻ ውስጥ እንደሚገኝ መርዛማ ዐረም ይበቅላል። 5 በሰማርያ የሚኖረው ሕዝብ፣ በቤትአዌን ስላለው የጥጃ ጣዖት ይፈራል፤ ሕዝቡም ያለቅስለታል፤ በክብሩ እጅግ ደስ ያላቸው ሁሉ፣ አመንዝራ ካህናትም እንደዚሁ ያለቅሱለታል፤ በምርኮ ከእነርሱ ተወስዷልና። 6 ለታላቁ ንጉሥ እንደ እጅ መንሻ፣ ወደ አሦር ይወሰዳል፤ ኤፍሬም ይዋረዳል፤ እስራኤልም ስለ ጣዖቱ ያፍራል። 7 ሰማርያና ንጉሧ፣ በውሃ ላይ እንዳለ ኵበት ተንሳፍፈው ይጠፋሉ። 8 የእስራኤል ኀጢአት የሆነው፣ የአዌን ማምለኪያ ኰረብታ ይጠፋል፤ እሾኽና አሜከላ ይበቅልባቸዋል፤ መሠዊያዎቻቸውንም ይወርሳል፤ በዚያ ጊዜ ተራሮችን፣ “ውደቁብን!” ኰረብቶችንም፣ “ሸፍኑን!” ይላሉ። 9 “እስራኤል ሆይ፤ ከጊብዓ ጊዜ ጀምሮ ኀጢአት ሠራችሁ፤ በዚያም ጸናችሁ፤ በጊብዓ የነበሩትን ክፉ አድራጊዎች፣ ጦርነት አልጨረሳቸውምን? 10 በፈለግሁ ጊዜ እቀጣቸዋለሁ፤ ስለ ድርብ ኀጢአታችሁም ይቀጧቸው ዘንድ፣ በእነርሱ ላይ ይሰበሰባሉ፤ 11 ኤፍሬም ማበራየት እንደምትወድድ፣ እንደ ተገራች ጊደር ነው፤ በተዋበ ጫንቃዋም ላይ፣ ቀንበርን አኖራለሁ፤ ኤፍሬምን እጠምዳለሁ፤ ይሁዳ ያርሳል፤ ያዕቆብም መሬቱን ያለሰልሳል። 12 ለራሳችሁ ጽድቅን ዝሩ፤ የጽኑ ፍቅርን ፍሬ ዕጨዱ፤ ዕዳሪውንም መሬት ዕረሱ፤ እርሱም መጥቶ፣ ጽድቅን በላያችሁ እስኪያዘንብ ድረስ፣ እግዚአብሔርን የምትፈልጉበት ጊዜ ነውና። 13 እናንተ ግን ክፋትን ዘራችሁ፤ ኀጢአትንም ዐጨዳችሁ፤ የሐሰትንም ፍሬ በላችሁ። በራሳችሁ ጕልበት፣ በተዋጊዎቻችሁም ብዛት ታምናችኋልና፣ 14 ሰልማን፣ ቤትአርብኤልን በጦርነት ጊዜ እንዳፈራረሰ፣ እናቶችንም ከልጆቻቸው ጋራ በምድር ላይ እንደ ፈጠፈጣቸው፣ ሽብር በሕዝብህ ላይ ይመጣል፤ ምሽጎችህም ሁሉ ይፈራርሳሉ። 15 ስለዚህ ቤቴል ሆይ፤ ክፋትሽ ታላቅ ስለ ሆነ፣ በአንቺም ላይ እንደዚሁ ይሆናል፤ ያ ቀን ሲደርስም፣ የእስራኤል ንጉሥ ፈጽሞ ይጠፋል።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.