ዘፍጥረት 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምቃየንና አቤል 1 አዳም ሚስቱን ሔዋንን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ቃየንን ወለደች፤ “በእግዚአብሔር ርዳታ ወንድ ልጅ አገኘሁ” አለች። 2 ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች። አቤል የበግ እረኛ፣ ቃየንም ዐራሽ ነበር። 3 በአንድ ወቅት፣ ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረበ። 4 አቤልም መጀመሪያ ከተወለዱት በጎቹ መካከል ስባቸውን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ 5 በቃየንና በመሥዋዕቱ ግን አልተደሰተም፤ ስለዚህ ቃየን ክፉኛ ተናደደ፤ ፊቱም ጠቈረ። 6 እግዚአብሔርም ቃየንን እንዲህ አለው፤ “ለምን ተናደድህ? ለምንስ ፊትህ ጠቈረ? 7 መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን? መልካም ባታደርግ ግን፣ ኀጢአት በደጅህ እያደባች ናት፤ ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፤ አንተ ግን ተቈጣጠራት።” 8 ቃየንም ወንድሙን አቤልን፣ “እስኪ ና፤ ወደ መስኩ እንውጣ” አለው፤ በመስኩም ሳሉ፣ ቃየን ወንድሙን አቤልን አጠቃው፤ ገደለውም። 9 ከዚያም፣ እግዚአብሔር ቃየንን፣ “ወንድምህ አቤል የት ነው?” አለው። ቃየንም፣ “አላውቅም፤ እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” ሲል መለሰ። 10 እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “ምንድን ነው ያደረግኸው? የወንድምህ ደም ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። 11 እንግዲህ የተረገምህ ነህ፤ የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፏን ከከፈተችው መሬት ትሰደዳለህ። 12 ብታርሳትም ፍሬዋን አትለግስህም፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች ትሆናለህ።” 13 ቃየንም እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “ቅጣቴ ልሸከመው ከምችለው በላይ ነው። 14 እነሆ፤ ዛሬ ከምድሪቱ አባረርኸኝ፤ ከፊትህም እሸሸጋለሁ፤ በምድር ላይ ኰብላይና ተንከራታች እሆናለሁ፤ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል።” 15 እግዚአብሔር ግን፣ “የለም! እንደርሱ አይሆንም፤ ማንም ቃየንን ቢገድል፣ ሰባት ዕጥፍ የበቀል ቅጣት ይቀበላል” አለው፤ ስለዚህ፣ ያገኘው ሁሉ እንዳይገድለው እግዚአብሔር በቃየን ላይ ምልክት አደረገለት። 16 ቃየንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄዶ፣ ከዔድን በስተምሥራቅ በምትገኝ ኖድ በተባለች ምድር ተቀመጠ። 17 ቃየን ሚስቱን ተገናኛት፤ እርሷም ፀንሳ ሔኖክን ወለደች። ቃየን የቈረቈረውን ከተማ በልጁ ስም ሔኖክ ብሎ ጠራው። 18 ሔኖክ ኢራድን ወለደ፤ ኢራድም መሑያኤልን፣ መሑያኤልም ማቱሣኤልን፣ ማቱሣኤልም ላሜሕን ወለደ። 19 ላሜሕ ሁለት ሚስቶች አገባ፤ የአንደኛዋ ስም ዓዳ፣ የሁለተኛዋም ሴላ ነበር። 20 ዓዳ ያባልን ወለደች፤ እርሱም በድንኳን ለሚኖሩ ከብት አርቢዎች አባት ነበረ። 21 ወንድሙም ዩባል ይባላል፤ እርሱም የበገና ደርዳሪዎችና የዋሽንት ነፊዎች አባት ነበረ። 22 ሴላም ደግሞ ቱባልቃይን የተባለ ወንድ ልጅ ነበራት፤ እርሱም ከብረትና ከናስ ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን እየቀረጸ የሚሠራ ነበር። የቱባልቃይን እኅት ናዕማ ትባል ነበር። 23 ላሜሕ ሚስቶቹን እንዲህ አላቸው፤ “ዓዳና ሴላ ሆይ ስሙኝ፤ የላሜሕ ሚስቶች ሆይ አድምጡኝ፤ አንድ ሰው ቢያቈስለኝ፣ ጕልማሳው ቢጐዳኝ፣ ገደልሁት፤ 24 ቃየንን የሚገድል ሰባት ጊዜ ቅጣት ካገኘው፣ የላሜሕ ገዳይማ ሰባ ሰባት ጊዜ ቅጣት ያገኘዋል።” 25 አዳም እንደ ገና ሚስቱን ተገናኛት፤ እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች። “ቃየን በገደለው በአቤል ፈንታ እግዚአብሔር ምትክ ሰጠኝ” ስትል ስሙን ሴት ብላ ጠራችው። 26 ለሴትም ደግሞ ወንድ ልጅ ተወለደለት፤ ስሙንም ሄኖስ አለው። በዚያም ዘመን ሰዎች የእግዚአብሔርን ስም መጥራት ጀመሩ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.