ዘፍጥረት 34 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየያዕቆብ ልጅ ተደፈረች 1 ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ሴት ልጅ ዲና፣ አንድ ቀን የዚያን አገር ሴቶች ለማየት ወጣች። 2 ሴኬም የተባለው የአገሩ ገዥ የኤዊያዊ የኤሞር ልጅ ባያት ጊዜ ይዞ በማስገደድ ደፈራት። 3 ልቡ በያዕቆብ ልጅ በዲና ተማረከ፤ ልጅቷንም በጣም ወደዳት፤ በጣፈጠም አንደበት አናገራት። 4 ሴኬምም አባቱን ኤሞርን፣ “ይህችን ልጅ አጋባኝ” አለው። 5 ያዕቆብ፣ ልጁን ዲናን ሴኬም እንዳስነወራት ሰማ፤ በዚህ ጊዜ ወንዶች ልጆቹ ከብቶቹን በመስክ ያግዱ ነበር፤ ያዕቆብም ልጆቹ እስኪመለሱ ድረስ ታግሦ ቈየ። 6 ከዚያም የሴኬም አባት ኤሞር፣ ያዕቆብን ሊያነጋግረው ወጣ። 7 የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም የተፈጸመውን ድርጊት እንደ ሰሙ ወዲያውኑ ከመስክ መጡ፤ ሴኬም መደረግ የማይገባውን አስነዋሪ ነገር በእስራኤል ላይ በመፈጸም፣ የያቆብን ልጅ ስለ ደፈረ ዐዘኑ፤ ክፉኛም ተቈጡ። 8 ኤሞር ግን እንዲህ አላቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልቡ በልጃችሁ ፍቅር ተነድፏል፤ እባካችሁ እንዲያገባት ፍቀዱለት። 9 በጋብቻ እንተሳሰር፤ ሴት ልጃችሁን ስጡን፤ የእኛንም ሴቶች አግቡ። 10 ዐብራችሁንም መኖር ትችላላችሁ፤ አገራችን አገራችሁ ናት፤ ኑሩባት፤ ነግዱባት፤ ሀብት ንብረትም አፍሩባት።” 11 ሴኬም ደግሞ የዲናን አባትና ወንድሞቿን እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ሞገስ ላግኝ እንጂ የተጠየቅሁትን ሁሉ እሰጣለሁ፤ 12 ጥሎሽ ብትሉኝ ጥሎሽ፣ ስጦታ ብትሉም የፈለጋችሁትን ያህል እሰጣለሁ፤ ብቻ ልጅቱን እንዳገባ ፍቀዱልኝ።” 13 የያዕቆብ ወንዶች ልጆችም፣ በእኅታቸው በዲና ላይ ስለ ተፈጸመው ነውር፣ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው፣ ለሴኬምና ለአባቱ ለኤሞር በተንኰል መልስ ሰጡ፤ 14 እንዲህም አሏቸው፤ “እኅታችንን ላልተገረዘ ሰው ብንሰጥ ውርደት ስለሚሆንብን፣ እንዲህ ያለውን ነገር አናደርገውም። 15 ሆኖም የምንስማማበት አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ ይህም ወንዶቻችሁን ሁሉ ገርዛችሁ እኛን የመሰላችሁ እንደ ሆነ ነው። 16 ከዚያ በኋላ ሴቶች ልጆቻችንን እንድርላችኋለን፤ ዐብረን እንኖራለን፤ አንድ ሕዝብም እንሆናለን። 17 በመገረዙ የማትስማሙ ከሆነ ግን ልጃችንን ይዘን እንሄዳለን።” 18 ያቀረቡትም ሐሳብ ለኤሞርና ለልጁ ለሴኬም መልካም መስሎ ታያቸው። 19 ከአባቱ ቤተ ሰብ ሁሉ እጅግ የተከበረው ይህ ወጣት የያዕቆብን ልጅ እጅግ ወድዷት ስለ ነበር፣ ያሉትን ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም። 20 ስለዚህ ኤሞርና ልጁ ሴኬም ይህንኑ ለወገኖቻቸው ለመንገር ወደ ከተማቸው በር ሄዱ፤ 21 እንዲህም አሏቸው፤ “እነዚህ ሰዎች ወዳጆቻችን ናቸው፤ በአገራችን እንዲኖሩ፣ ተዘዋውረውም እንዲነግዱ እንፍቀድላቸው፤ ምድሪቱ እንደሆን ለእኛም ለእነርሱም ትበቃለች። ሴቶች ልጆቻቸውን እናገባለን፤ እነርሱም የእኛን ሴቶች ያገባሉ። 22 ሆኖም ሰዎቹ ከእኛ ጋራ እንደ አንድ ሕዝብ ሆነው ዐብረውን ለመኖር ፈቃደኞች የሚሆኑት፣ የእኛ ወንዶች እንደ እነርሱ የተገረዙ እንደ ሆነ ብቻ ነው። 23 ታዲያ እንዲህ ብናደርግ ከብታቸው ንብረታቸው፣ እንስሶቻቸው ሁሉ የእኛው ይሆኑ የለምን? ስለዚህ ባሉት እንስማማ፤ እነርሱም ዐብረውን ይኑሩ።” 24 ከከተማዪቱ በር ውጭ የተሰበሰቡት ሁሉ በኤሞርና በልጁ በሴኬም ሐሳብ ተስማሙ፤ በከተማዪቱም ያሉት ወንዶች ሁሉ ተገረዙ። 25 በሦስተኛውም ቀን የሁሉም ቍስል ገና ትኵስ ሳለ ከያዕቆብ ልጆች ሁለቱ፣ የዲና ወንድሞች ስምዖንና ሌዊ፣ ሰይፋቸውን መዝዘው በድንገት ወደ ከተማዪቱ ገብተው ወንዶቹን በሙሉ ገደሏቸው። 26 ኤሞርንና ሴኬምንም በሰይፍ ገድለው፣ እኅታቸውን ዲናን ከሴኬም ቤት አውጥተው ይዘዋት ተመለሱ። 27 የያዕቆብ ልጆች ሁሉ በሬሳ ላይ እየተረማመዱ እኅታቸው የተደፈረችበትን ከተማ ዘረፉ። 28 የበግና የፍየል መንጎቻቸውን፣ ከብቶቻቸውንና አህዮቻቸውን እንዲሁም በከተማዪቱና በአካባቢው የሚገኘውን ንብረታቸውን ሁሉ ወሰዱባቸው፤ 29 ሀብታቸውን ሁሉ ዘርፈው ሴቶቻቸውንና ሕፃኖቻቸውን ሁሉ ማርከው በየቤቱ ያገኙትን ሁሉ ይዘው ሄዱ። 30 ያዕቆብም ስምዖንና ሌዊን እንዲህ አላቸው፤ “በዚህ አገር በሚኖሩት በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ዘንድ እንደ ጥንብ አስቈጠራችሁኝ፤ ጭንቀትም እንዲደርስብኝ አድርጋችኋል። እኛ በቍጥር አነስተኞች ነን፤ ተባብረው ቢነሡብኝና ቢያጠቁኝ እኔና ቤተ ሰቤ መጥፋታችን አይደለምን?” 31 እነርሱ ግን፣ “ታዲያ፣ እኅታችንን እንደ ዝሙት ዐዳሪ ይድፈራት?” አሉት። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.