Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘፍጥረት 13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የአብራምና የሎጥ መለያየት

1 አብራም ሚስቱንና ንብረቱን ሁሉ ይዞ ከግብጽ ወደ ኔጌብ ሄደ፤ ሎጥም ዐብሮት ነበረ።

2 አብራም በከብት፣ በብርና በወርቅ እጅግ በልጽጎ ነበር።

3 አብራም ከኔጌብ ተነሥቶ እስከ ቤቴል ተጓዘ፤ ቀድሞ በቤቴልና በጋይ መካከል ድንኳኑን ከተከለበት፣

4 ለመጀመሪያ ጊዜም መሠዊያ ካቆመበት ስፍራ ደረሰ፤ በዚያም የእግዚአብሔርን ስም ጠራ።

5 ከአብራም ጋራ ዐብሮት ይጓዝ የነበረው ሎጥ በጎች፣ ከብቶችና ድንኳኖች ነበሩት።

6 ሆኖም ሁለቱ አንድ ላይ ሲኖሩ ስፍራው አልበቃቸውም፤ ንብረታቸው እጅግ ብዙ ስለ ነበር፣ ዐብረው መኖር አልቻሉም።

7 ይህም በመሆኑ በአብራምና በሎጥ መንጎች እረኞች መካከል ጠብ ተፈጠረ። በዚያ ዘመን ከነዓናውያንና ፌርዛውያን በዚያው አገር ይኖሩ ነበር።

8 አብራምም ሎጥን እንዲህ አለው፤ “እኛ ወንድማማቾች ነንና፣ በአንተና በእኔ ወይም በእረኞቻችን መካከል ጠብ ሊኖር አይገባም።

9 ይኸው እንደምታየው አገሩ ሰፊ ነው፤ ብንለያይ ይሻላል። አንተ ግራውን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፤ አንተ ቀኙን ብትመርጥ፣ እኔ ወደ ግራ አመራለሁ።”

10 ሎጥ ዐይኑን አቅንቶ ሲመለከት፣ የዮርዳኖስ ረባዳ ሜዳ እንደ እግዚአብሔር ገነት፣ በዞዓር አቅጣጫ እንዳለው እንደ ግብጽ ምድር ውሃማ ቦታ ሆኖ አገኘው። እንዲህም የነበረው እግዚአብሔር የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ከማጥፋቱ በፊት ነው።

11 ሎጥ የዮርዳኖስን ረባዳ ሜዳ በሙሉ መርጦ ወደ ምሥራቅ አመራ፤ ሁለቱ ሰዎች በዚሁ ተለያዩ።

12 አብራም መኖሪያውን በከነዓን ምድር አደረገ፤ ሎጥ ግን በረባዳው ሜዳ ውስጥ ባሉት ከተሞች መካከል በሰዶም አቅራቢያ ድንኳኑን ተከለ።

13 የሰዶም ሰዎች ግን ክፉዎችና በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ኃጥኣን ነበሩ።

14 ሎጥ ከተለየው በኋላ እግዚአብሔር አብራምን እንዲህ አለው፤ “ካለህበት ስፍራ ቀና ብለህ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ፣ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ ተመልከት፤

15 ዐይንህ የሚያየውን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁ።

16 ዘርህን እንደ ምድር ትቢያ አበዛዋለሁ፤ ማንም የምድርን ትቢያ ሊቈጥር እንደማይችል ሁሉ የአንተም ዘር የማይቈጠር ይሆናል።

17 እንግዲህ ምድሪቱን ስለምሰጥህ ተነሣ፤ በርዝመቷም፣ በስፋቷም ተመላለስባት።”

18 አብራምም ድንኳኑን ነቀለ፤ ሄዶም ኬብሮን በሚገኙት ትልልቅ የመምሬ ዛፎች አጠገብ ተቀመጠ፤ በዚያም ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች