Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መክብብ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ምድራዊ ደስታ ከንቱ ነው

1 እኔም በልቤ፣ “መልካም የሆነውን ለማወቅ፣ በተድላ እፈትንሃለሁ” አልሁ፤ ነገር ግን ያም ከንቱ ነበረ።

2 ደግሞም፣ “ሣቅ ሞኝነት ነው፤ ተድላስ ምን ይጠቅማል?” አልሁ።

3 አሁንም አእምሮዬ በጥበብ እየመራኝ ራሴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሠኘት፣ ሞኝነትንም ለመያዝ ሞከርሁ፤ ሰዎች በዐጭር የሕይወት ዘመናቸው ከሰማይ በታች ባለው ላይ ቢሠሩት ሊጠቅማቸው የሚችል ምን እንደ ሆነ ለማየት ፈለግሁ።

4 ታላላቅ ነገሮችን አከናወንሁ፤ ለራሴ ቤቶችን ሠራሁ፤ ወይንንም ተከልሁ፤

5 አትክልትን ተከልሁ፤ የመዝናኛ ስፍራዎችን አዘጋጀሁ፤ በእነዚህም ላይ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶችን ሁሉ ተከልሁባቸው፤

6 የሚለመልሙ ዛፎችን፣ ለቦይ የሚሆኑ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ሠራሁ።

7 ወንድና ሴት ባሪያዎችን ገዛሁ፤ በቤቴም የተወለዱ ሌሎች ባሪያዎች ነበሩኝ። ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ይልቅ ብዙ የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎች ነበሩኝ።

8 ለራሴም ብርንና ወርቅን፣ የነገሥታትና የአውራጃዎችን ሀብት አካበትሁ፤ ወንድና ሴት አዝማሪዎች፣ የሰው መደሰቻ የሆኑ ቅምጦች ነበሩኝ።

9 ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሆንሁ፤ በዚህ ሁሉ ጥበቤ ከእኔ ጋራ ነበረች።

10 ዐይኔ የፈለገውን ሁሉ አልከለከልሁትም፤ ለልቤም ምድራዊ ደስታን አልነፈግሁትም፤ ልቤ በሠራሁት ሁሉ ደስ አለው፤ ይህም የድካሜ ሁሉ ዋጋ ነበረ።

11 ሆኖም እጆቼ የሠሩትን ሁሉ፣ ለማግኘትም የደከምሁትን ድካም ሁሉ ሳስብ፣ ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፤ ከፀሓይ በታች ምንም ትርፍ አልነበረም።


ጥበብና ሞኝነት ከንቱ ናቸው

12 ከዚያም ጥበብን፣ እብደትንና ሞኝነትን ለመመርመር ሐሳቤን መለስሁ፤ አስቀድሞ ከተደረገው በቀር፣ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል?

13 ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ ሁሉ፣ ጥበብም ከሞኝነት እንደሚበልጥ ተመለከትሁ።

14 የጠቢብ ሰው ዐይኖች ያሉት በራሱ ውስጥ ነው፤ ሞኝ ግን በጨለማ ውስጥ ይራመዳል፤ ሆኖም የሁለቱም ዕድል ፈንታ፣ አንድ መሆኑን ተገነዘብሁ።

15 ከዚያም በልቤ፣ “የሞኙ ዕድል ፈንታ በእኔም ላይ ይደርሳል፤ ታዲያ ጠቢብ በመሆኔ ትርፌ ምንድን ነው?” አልሁ። በልቤም፣ “ይህም ደግሞ ከንቱ ነው” አልሁ።

16 ጠቢቡም ሰው እንደ ሞኙ ለዘላለም አይታወስምና፤ በሚመጡት ዘመናት ሁለቱም ይረሳሉ። ለካ፣ ጠቢቡም እንደ ሞኙ መሞቱ አይቀርም!


ጥረት ከንቱ ነው

17 ስለዚህ ከፀሓይ በታች የሚሠራው ሥራ አሳዛኝ ስለ ሆነብኝ ሕይወትን ጠላሁ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።

18 ከፀሓይ በታች የደከምሁበትን ነገር ሁሉ ጠላሁት፣ ከኋላዬ ለሚመጣው ሰው የግድ እተውለታለሁና።

19 እርሱ ጠቢብ ወይም ሞኝ ይሆን እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ሆኖም ከፀሓይ በታች ድካሜንና ችሎታዬን ባፈሰስሁበት ሥራ ሁሉ ላይ ባለቤት ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

20 ስለዚህ ከፀሓይ በታች በደከምሁበት ነገር ሁሉ ላይ ልቤ ተስፋ መቍረጥ ጀመረ፤

21 ምክንያቱም ሰው ሥራውን በጥበብ፣ በዕውቀትና በብልኀት ሠርቶ፣ ከዚያ ያለውን ሁሉ ለሌላ ላልለፋበት ሰው ይተውለታል። ይህም ደግሞ ከንቱና ትልቅ ጕዳት ነው።

22 ሰው ከፀሓይ በታች በሚደክምበት ጥረትና ልፋት ሁሉ ትርፉ ምንድን ነው?

23 በዘመኑ ሁሉ ሥራው ሥቃይና ሐዘን ነው፤ በሌሊትም እንኳ ቢሆን አእምሮው አያርፍም። ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

24 ለሰው ከመብላትና ከመጠጣት፣ በሥራውም ከመርካት ሌላ የሚሻለው ነገር የለውም፤ ይህም ደግሞ ከአምላክ እጅ እንደሚሰጥ አየሁ፤

25 ከርሱ ዘንድ ካልሆነ ማን መብላትና መደሰት ይችላል?

26 አምላክ፣ ደስ ለሚያሠኘው ሰው ጥበብን፣ ዕውቀትንና ደስታን ይሰጠዋል። ለኀጢአተኛ ግን፣ አምላክን ደስ ለሚያሠኘው ይተውለት ዘንድ፣ ሀብትን የመሰብሰብና የማከናወን ተግባር ይሰጠዋል። ይህም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች