Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መክብብ 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 የሞቱ ዝንቦች ሽቱን እንደሚያገሙ፣ ትንሽ ሞኝነትም ጥበብንና ክብርን ያቀልላል።

2 የጠቢብ ልብ ወደ ቀኝ፣ የሞኝ ልብ ግን ወደ ግራ ያዘነብላል።

3 ሞኝ በጐዳና ሲሄድ ልበ ቢስ ነው፤ ጅል መሆኑንም ለማንም ይገልጻል።

4 የገዥ ቍጣ በተነሣብህ ጊዜ፣ ስፍራህን አትልቀቅ፤ ትዕግሥት ታላቁን ጥፋት ጸጥ ያደርጋልና።

5 ከፀሓይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፤ ይህም ከገዥ የሚወጣ ስሕተት ነው፤

6 ሞኞች በብዙ የክብር ስፍራዎች ሲቀመጡ፣ ሀብታሞች ግን በዝቅተኛ ስፍራ ሆነዋል።

7 መሳፍንት እንደ ባሮች በእግራቸው ሲሄዱ፣ ባሮች ፈረስ ላይ ተቀምጠው አይቻለሁ።

8 ጕድጓድን የሚምስ ራሱ ይገባበታል፤ ቅጥርንም የሚያፈርስ እባብ ይነድፈዋል።

9 ድንጋይ የሚፈነቅል ይጐዳበታል፤ ግንድንም የሚፈልጥ አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም።

10 መጥረቢያ ቢደንዝ፣ ጫፉም ባይሳል፣ ብዙ ጕልበት ይጨርሳል፤ ብልኀት ግን ለውጤት ያበቃል።

11 እባብ በድግምት ከመፍዘዙ በፊት ቢነድፍ፣ ለደጋሚው ምንም አይጠቅመውም።

12 ከጠቢብ አፍ የሚወጣ ቃል ባለሞገስ ነው፤ ሞኝ ግን በገዛ ከንፈሩ ይጠፋል፤

13 ቃሉ በመጀመሪያ ሞኝነት ነው፤ በመጨረሻም ደግሞ ክፉ እብደት ነው፤

14 ሞኙም ቃልን ያበዛል። የሚመጣውን የሚያውቅ ሰው የለም፤ ከርሱ በኋላ የሚሆነውንስ ማን ሊነግረው ይችላል?

15 የሞኝ ሥራ ራሱን ያደክመዋል፤ ወደ ከተማ የሚወስደውንም መንገድ አያውቅም።

16 አንቺ፣ ንጉሥሽ ልጅ የሆነ፣ መሳፍንትሽም በጧት ግብዣ የሚያደርጉ ምድር ሆይ፤ ወዮልሽ!

17 አንቺ ንጉሥሽ ከተከበረው ዘር የሆነ፣ ለመስከር ሳይሆን ለብርታት፣ በተገቢው ጊዜ የሚበሉ መኳንንት ያሉሽ ምድር ሆይ፤ ብፁዕ ነሽ።

18 ሰው ሰነፍ ከሆነ ጣራው ይዘብጣል፤ እጆቹም ካልሠሩ ቤቱ ያፈስሳል።

19 ግብዣ ለሣቅ ያዘጋጃል፤ ወይንም ሕይወትን ያስደስታል፤ ገንዘብም ካለ ሁሉ ነገር አለ።

20 በሐሳብህም እንኳ ንጉሥን አትንቀፍ፤ በመኝታ ክፍልህም ባለጠጋን አትርገም፤ የሰማይ ወፍ ቃልህን ልትወስድ፣ የምትበረዋም ወፍ የምትለውን ልታደርስ ትችላለችና።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች