Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ዘዳግም 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


እግዚአብሔርን ውደድ፤ ታዘዘውም

1 እንግዲህ አምላክህን እግዚአብሔርን ውደድ፤ ግዴታውን፣ ሥርዐቱን፣ ሕጉንና ትእዛዙን ሁልጊዜ ጠብቅ።

2 የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ተግሣጽ ይኸውም ግርማውን፣ ብርቱ እጁንና የተዘረጋች ክንዱን ያዩትና የተለማመዱት ልጆቻችሁ ሳይሆኑ እናንተ እንደ ሆናችሁ ዛሬ አስታውሱ፤

3 በግብጽ መካከል፣ በግብጽ ንጉሥ በፈርዖንና በመላው አገሩ ላይ ያደረጋቸውን ምልክቶችና የሠራቸውን ነገሮች፣

4 በግብጻውያን ሰራዊት፣ በፈረሶቻቸውና በሠረገሎቻቸው ላይ፣ እናንተን ባሳደዷችሁ ጊዜ በቀይ ባሕር ውሃ እንዴት እንዳሰጠማቸውና እግዚአብሔር ፈጽሞ እንዴት እንዳጠፋቸው አስታውሱ፤

5 ከምድረ በዳው አንሥቶ እዚህ እስከምትደርሱ ድረስ፣ ለእናንተ ያደረገላችሁን ያዩት ልጆቻችሁ አልነበሩም፤

6 የሮቤል ልጅ የኤልያብ ልጆች የሆኑትን ዳታንና አቤሮንን ከነቤተ ሰቦቻቸው፣ ከነድንኳናቸውና ከነእንስሳታቸው በመላው እስራኤል መካከል ምድር እንዴት አፏን ከፍታ እንደ ዋጠቻቸው እነርሱ አላዩም።

7 የእናንተ ዐይኖች ግን እግዚአብሔር ያደረጋቸውን ሥራዎች ሁሉ አይተዋል።

8 ስለዚህ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ወደምትወርሷት ምድር ለመግባትና ለመያዝ ብርታት እንድታገኙ፣ ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች ሁሉ ጠብቁ፤

9 ለአባቶቻቸውና ለዘሮቻቸው እግዚአብሔር ሊሰጣቸው በማለላቸው፣ በዚያች ማርና ወተት በምታፈስሰው ምድር ረዥም ዕድሜ ትኖሩ ዘንድ፣

10 የምትገባባት ምድር እንደ ወጣህባትና ዘርህን ዘርተህባት በእግርህ ውሃ እንዳጠጣሃት የአትክልት ቦታ እንደ ግብጽ ምድር አይደለችም።

11 ዮርዳኖስን ተሻግረህ ልትወርሳት ያለችው ምድር ግን፣ ከሰማይ ዝናብ የምትጠጣ፣ ተራሮችና ሸለቆች ያሉባት ምድር ናት።

12 ይህች ምድር አምላክህ እግዚአብሔር የሚንከባከባት፣ ከዓመቱ መጀመሪያ እስከ ዓመቱ መጨረሻ የአምላክህ የእግዚአብሔር ዐይን ምን ጊዜም የማይለያት ናት።

13 ዛሬ እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዞች በታማኝነት ብትጠብቁ፣ ይኸውም አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትወድዱና በፍጹም ልባችሁ፣ በፍጹም ነፍሳችሁም እርሱን በማገልገል በታማኝነት ብትጠብቁ፣

14 እህልህን፣ ወይንህንና ዘይትህን እንድትሰበስብ የበልጉንና የክረምቱን ዝናብ በምድርህ ላይ በየወቅቱ አዘንባለሁ።

15 በሜዳ ላይ ለከብቶችህ ሣር እሰጣለሁ፤ አንተም ትበላለህ፤ ትጠግባለህም።

16 ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ተታልላችሁ ሌሎች አማልክትን ታመልካላችሁ፤ ትሰግዳላችሁም።

17 ከዚያም የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ይነድዳል፤ እርሱም ዝናብ እንዳይዘንብ፣ ምድሪቱም ፍሬ እንዳትሰጥ ሰማያትን ይዘጋል፤ እናንተም እግዚአብሔር ከሚሰጣችሁ ከመልካሚቱ ምድር ወዲያውኑ ትጠፋላችሁ።

18 እነዚህን ቃሎቼን፣ በልባችሁና በአእምሯችሁ አኑሯቸው፤ በእጆቻችሁ ላይ ምልክት አድርጋችሁ እሰሯቸው፣ በግንባራችሁም ላይ ይሁኑ።

19 ልጆቻችሁንም አስተምሯቸው፤ በቤትህ ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛና ስትነሣም ስለ እነርሱ ተናገር።

20 በቤትህ መቃኖችና በግቢህም በሮች ላይ ጻፋቸው፤

21 ይህን ካደረጋችሁ፣ እግዚአብሔር ለአባቶቻችሁ ለመስጠት በማለላቸው ምድር የእናንተና የልጆቻችሁ ዘመን ከምድር በላይ ያሉ ሰማያትን ርቀት ያህል ይሆናል።

22 አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፣ በመንገዶቹም ሁሉ ትሄዱና ከርሱም ጋራ ትጣበቁ ዘንድ እንድትከተሏቸው የምሰጣችሁን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ብትጠብቁ፣

23 እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ሁሉ ከፊታችሁ ያስወጣቸዋል፤ እናንተም፣ ከእናንተ ይልቅ ታላላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ ታስለቅቃላችሁ።

24 በእግራችሁ የምትረግጡት ስፍራ ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ግዛታችሁም ከምድረ በዳው እስከ ሊባኖስ፣ ከኤፍራጥስ ወንዝ አንሥቶ በስተምዕራብ እስካለው ባሕር ይደርሳል።

25 ማንም ሰው ሊቋቋማችሁ አይችልም፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ ተስፋ መሠረት ማስደንገጣችሁንና መፈራታችሁን በምትሄዱበት በየትኛውም ምድር ሁሉ ላይ ያሳድራል።

26 እነሆ፤ ዛሬ በረከትንና መርገምን በፊታችሁ አኖራለሁ፤

27 በረከቱ ዛሬ የምሰጣችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች ስትፈጽሙ ሲሆን፣

28 መርገሙ ደግሞ፣ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የማትፈጽሙ፣ የማታውቋቸውንም ሌሎች አማልክት ለመከተል እኔ ከማዝዛችሁ መንገድ የምትወጡ ከሆነ ነው።

29 ልትወርሳት ወደምትሄድባት ምድር አምላክህ እግዚአብሔር በሚያስገባህ ጊዜ በረከቱን በገሪዛን ተራራ፣ መርገሙን ደግሞ በጌባል ተራራ ላይ ታሰማለህ።

30 እነዚህ ተራሮች የሚገኙት ከዮርዳኖስ ማዶ ፀሓይ በምትጠልቅበት አቅጣጫ ካለው መንገድ በስተምዕራብ በዓረባ በሚኖሩ የከነዓናውያን ምድር ውስጥ ከጌልገላ ፊት ለፊት፣ በሞሬ ታላላቅ ዛፎች አጠገብ አይደለምን?

31 አምላካችሁ እግዚአብሔር በሚሰጣችሁ ምድር ትገቡባትና ትወርሷት ዘንድ ዮርዳኖስን ልትሻገሩ ስለ ሆነ፣ ምድሪቱን ወርሳችሁ በምትኖሩባት ጊዜ፣

32 ዛሬ በፊታችሁ እኔ ያስቀመጥኋቸውን ሥርዐቶችና ሕጎች ሁሉ ለመፈጸም ተጠንቀቁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች