Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

2 ሳሙኤል 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የገባዖናውያን ብቀላ

1 በዳዊት ዘመነ መንግሥት፣ በተከታታይ ለሦስት ዓመት ራብ ሆነ፤ ስለዚህ ዳዊት እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም፣ “ሳኦል ገባዖናውያንን ስለ ገደለ፣ እርሱና ቤቱ የደም ዕዳ አለባቸው” አለ።

2 ንጉሡ ገባዖናውያንን ጠርቶ አነጋገራቸው። ገባዖናውያን ከአሞራውያን የተረፉ እንጂ ከእስራኤል ወገን አልነበሩም፤ እስራኤላውያን ሊጠብቋቸው ቢምሉላቸውም፣ ሳኦል ግን ለእስራኤልና ለይሁዳ ካለው ቅናት የተነሣ ሙሉ በሙሉ ሊያጠፋቸው ፈልጎ ነበር፤

3 ዳዊትም ገባዖናውያንን፣ “ምን ላድርግላችሁ? የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ማስተስረያውን ምን ማድረግ አለብኝ?” ሲል ጠየቃቸው።

4 ገባዖናውያንም፣ “ከሳኦልም ሆነ ከቤተ ሰቡ ብር ወይም ወርቅ የመጠየቅ መብት የለንም፤ እንዲሁም ከእስራኤል ማንንም ለመግደል መብት የለንም” ብለው መለሱለት። ዳዊትም፣ “ታዲያ ምን ላድርግላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

5 እነርሱም ንጉሡን፣ “እንድንፈራርስና በእስራኤልም ውስጥ በየትኛውም ስፍራ እንዳንኖር ካጠፋንና ደባ ከፈጸመብን ሰው

6 ከርሱ ዘሮች ሰባት ወንዶች ልጆች ይሰጠን፤ እኛም ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ በእግዚአብሔር ፊት እንስቀላቸው” ብለው መለሱለት። ስለዚህ ንጉሡ፣ “ዕሺ እሰጣችኋለሁ” አለ።

7 ንጉሥ ዳዊት በራሱና በሳኦል ልጅ በዮናታን መካከል በእግዚአብሔር ፊት ስላደረጉት መሐላ ሲል የሳኦልን ልጅ፣ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን ከሞት አተረፈ።

8 ነገር ግን ንጉሡ፣ የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ለሳኦል የወለደቻቸውን ሁለቱን ወንዶች ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን፤ የሳኦል ልጅ ሜሮብ ለመሓላታዊው ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደችለትን ዐምስት ወንዶች ልጆች ጭምር ወሰደ፤

9 ለገባዖናውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ገድለው በኰረብታው ላይ በእግዚአብሔር ፊት ሰቀሏቸው። ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፤ የተገደሉትም በመከሩ ወራት የመጀመሪያ ቀኖች፣ የገብስ ዐጨዳ በተጀመረበት ዕለት ነበር።

10 የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ፣ በቋጥኝ ላይ ለራሷ አነጠፈች፤ ከመከር ወቅት መጀመሪያ አንሥቶ ዝናብ ከሰማይ በሬሳዎቹ ላይ እስከ ወረደ ጊዜ ድረስ፣ ቀን የሰማይ ወፎች ሌሊት የዱር አራዊት እንዲነኳቸው አልፈቀደችም፤

11 የሳኦል ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ዳዊት በሰማ ጊዜ፣

12 ሄዶ የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች ወሰደ፤ የኢያቢስ ገዦች፣ ፍልስጥኤማውያን ሳኦልን በጊልቦዓ ከገደሉ በኋላ እነርሱን ከሰቀሉት ከቤትሳን አደባባይ በድብቅ ወስደዋቸው ነበር።

13 ዳዊትም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም ከዚያ አመጣ፤ እንዲሁም የእነዚያን የተገደሉትን ሰዎች ዐፅም ሰበሰቡ።

14 የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን ዐፅም በብንያም አገር ጼላ በተባለ ስፍራ በሳኦል አባት በቂስ መቃብር ቀበሩት፤ ንጉሡ ያዘዘውንም ሁሉ አደረጉ። ከዚያ በኋላም ስለ ምድሪቱ የቀረበውን ጸሎት እግዚአብሔር ሰማ።


በፍልስጥኤማውያን ላይ የተደረገ ጦርነት
21፥15-22 ተጓ ምብ – 1ዜና 20፥4-8

15 እንደ ገና በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤል መካከል ጦርነት ተደረገ። ዳዊትም ከሰዎቹ ጋራ ሆኖ ፍልስጥኤማውያንን ለመውጋት ወረደ፤ በዚያም ደከመው።

16 ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነ ይሽቢብኖብ የተባለ፣ የናስ ጦሩ ሦስት መቶ ሰቅል የሚመዝንና አዲስ ሰይፍ የታጠቀ ሰው ነበረ፤ እርሱም ዳዊትን ለመግደል ዐሰበ።

17 የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን ዳዊትን ለመታደግ መጣ፤ ፍልስጥኤማዊውንም ወግቶ ገደለው። ከዚያም የዳዊት ሰዎች፣ “የእስራኤል መብራት እንዳይጠፋ ከእንግዲህ አንተ ከእኛ ጋራ ወደ ጦርነት መውጣት የለብህም” ብለው ማሉለት።

18 ከዚህ በኋላ ጎብ በተባለ ስፍራ ከፍልስጥኤማውያን ጋራ ሌላ ጦርነት ተደረገ። በዚያ ጊዜም ኩሳታዊው ሴቦካይ፣ ከራፋይም ዘሮች አንዱ የሆነውን፣ ሳፍን ገደለው።

19 ጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋራ በተደረገ ሌላ ጦርነትም፣ የቤተ ልሔሙ የዓሬዓርጊም ልጅ ኤልያናን፣ የጦሩ ዘንግ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የሆነውን የጋት ሰው የጎልያድን ወንድም ገደለው።

20 እንደ ገና ጋት ላይ በተደረገው ጦርነት በእያንዳንዱ እጁና በእያንዳንዱ እግሩ ስድስት ስድስት ጣቶች በአጠቃላይ ሃያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ግዙፍ ሰው ነበረ፤ እርሱም ደግሞ ከራፋይም ዘር ነበረ።

21 እርሱም እስራኤልን በተገዳደረ ጊዜ፣ የዳዊት ወንድም የሳምዓ ልጅ ዮናታን ገደለው።

22 እነዚህ አራቱ በጋት የራፋይም ዘሮች የነበሩ ናቸው፤ እነርሱም በዳዊትና በሰዎቹ እጅ ወደቁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች