ሶፎንያስ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሩሳሌም በደልና ወደ ፊት የምታገኘው ቤዛነት 1 በኃጢአት ሕዝብዋን በመጨቈን ለረከሰች፥ ዐመፀኛ ለሆነችው ለኢየሩሳሌም ከተማ ወዮላት! 2 ማንንም አታዳምጥም፤ ተግሣጽም አትቀበልም፤ በእግዚአብሔር አትተማመንም፤ ወደ አምላክዋም አትቀርብም። 3 መሪዎችዋ እንደሚያገሡ አንበሶች ናቸው፤ ዳኞችዋም ለነገ ሳያስተርፉ ያገኙትን ሁሉ በልተው እንደሚጨርሱ እንደ ተራቡ የማታ ተኲላዎች ናቸው። 4 ነቢያትዋ በትዕቢት የተወጠሩና በተንኰል የተሞሉ ናቸው፤ ካህናትዋ የተቀደሰውን ያረክሳሉ፤ በሕግም ላይ ያምፃሉ። 5 ጻድቁ እግዚአብሔር በርስዋ ውስጥ አለ፤ እርሱ ስሕተት አያደርግም፤ እርሱ በየቀኑ ፍርድን ይሰጣል፤ በየማለዳው ይህን ከማድረግ አይቈጠብም፤ ክፉ አድራጊ ሕዝብ ግን ኀፍረት የለውም። 6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሕዛብ “መንግሥታትን አጠፋሁ፤ ምሽጎቻቸውን አፈራረስኩ፤ መንገዶቻቸውን ማንም የማይተላለፍባቸው ባዶ አድርጌአቸዋለሁ፤ ከተሞቻቸውን ሕዝብ የሌለባቸው፥ ማንም የማይኖርባቸው ባድማ አድርጌአቸዋለሁ። 7 እኔም ይህን ሁሉ በማድረጌ ‘ሕዝቤ ያከብረኛል፤ ተግሣጼንም ይቀበላል፤ የደረሰበትንም ተግሣጽ ሁሉ አይረሳም’ ብዬ ነበር፤ ሕዝቤ ግን እየባሰበት ሄደ፤ በክፉ ሥራውም ረከሰ።” 8 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ጥቂት ታገሡ፤ በእነርሱ ላይ የምፈርድበት ጊዜ ይመጣል፤ ሕዝቦችንና መንግሥታትን ሰብስቤ ኀይለኛ ቊጣዬን አወርድባቸዋለሁ፤ ከቊጣዬም ኀይለኛነት የተነሣ መላዋ ምድር ትጠፋለች። 9 “በዚያን ጊዜ ሕዝቦች ንጹሕ ንግግር እንዲናገሩ አደርጋለሁ፤ ይህንንም የማደርገው ሁሉም የእኔን የእግዚአብሔርን ስም እንዲጠሩና በአንድነት እንዲያገለግሉኝ ነው። 10 በስደት ተበታትነው የሚኖሩት ወገኖቼ ያመልኩኝ ዘንድ ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ መባ ይዘውልኝ ይመጣሉ። 11 ትዕቢተኞችንና ትምክሕተኞችን ከመካከላችሁ ስለማስወግድ በእኔ ላይ ስለ ፈጸማችሁት በደል በዚያን ጊዜ አታፍሩበትም፤ ከእንግዲህ ወዲህ በተቀደሰው ተራራዬ ላይ አትታበዩም። 12 ከመካከላችሁ ራሳቸውን ዝቅ ያደረጉ ትሑታን ሰዎችን አስቀራለሁ፤ እነርሱም በእኔ የሚታመኑና የእኔንም ርዳታ የሚሹ ይሆናሉ። 13 ከምርኮ የተረፉት የእስራኤል ሕዝብ በማንም ላይ ክፉ ነገር አያደርጉም፤ ሐሰት አይናገሩም፤ በአንደበታቸውም አያታልሉም፤ ስለዚህም ተመግበው በሰላም ይኖራሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም።” የደስታ መዝሙር 14 የጽዮን ልጅ ሆይ! ዘምሪ! የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ዘምሩ! እልልም በሉ! የኢየሩሳሌምም ሕዝብ ሆይ! በሙሉ ልባችሁ ደስ ይበላችሁ! ሐሴትም አድርጉ። 15 እግዚአብሔር በእናንተ ላይ ያስተላለፈውን የቅጣት ፍርድ አንሥቶላችኋል፤ ጠላቶቻችሁንም አስወግዶላችኋል፤ የእስራኤል ንጉሥ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት ይደርስብናል ብላችሁ አትፈሩም። 16 በዚያን ጊዜ ስለ ኢየሩሳሌም እንደዚህ ይባልላታል፤ “የጽዮን ከተማ ሆይ! አትፍሪ! ክንዶችሽም አይዛሉ! 17 እግዚአብሔር አምላክሽ ከአንቺ ጋር ነው፤ በኀይሉም ድልን ያጐናጽፍሻል፤ እግዚአብሔር በአንቺ ደስ ይለዋል፤ በፍቅሩም ያድስሻል፤ ሕዝቦች በበዓል ቀን በመዝሙር እንደሚያደርጉት፥ እርሱ በአንቺ ይደሰታል።” 18 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በበዓል ቀን እንደሚደረገው የደስታ ስሜት እንዲሰማሽ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ምንም ኀፍረት አይደርስብሽም። 19 የሚያስጨንቁሽን ሁሉ በዚያን ጊዜ እቀጣለሁ፤ ያነከሱትን ሁሉ አድናለሁ፤ የተገለሉትን መልሼ እሰበስባቸዋለሁ፤ ኀፍረት እንዲሰማቸው ተደርገው በነበሩበት ቦታ ሁሉ ኀፍረታቸውን ወደ ምስጋናና ክብር እለውጣለሁ።” 20 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ጊዜ ሰብስቤ ወደ ሀገራችሁ እመልሳችኋለሁ፤ ንብረታችሁን ሁሉ ዐይናችሁ እያየ በምመልስላችሁ ጊዜ በምድር ሕዝቦች ሁሉ ፊት ዝነኞችና የተመሰገናችሁ ትሆናላችሁ።” |