Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሮሜ 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የአይሁድ አለማመን

1 እንግዲህ አይሁዳዊ ከአሕዛብ የሚበልጠው በምንድን ነው? የመገረዝስ ጥቅሙ ምንድን ነው?

2 በእርግጥ አይሁዳዊ መሆን በብዙ መንገድ ብልጫ አለው፤ ዋናው ነገር እግዚአብሔር ቃሉን ለአይሁድ ዐደራ መስጠቱ ነው።

3 ታዲያ፥ ከአይሁድ አንዳንዶቹ ታማኞች ሆነው ባይገኙ፥ የእነርሱ ታማኞች አለመሆን የእግዚአብሔርን ታማኝነት ያስቀራልን?

4 ከቶ አያስቀርም! “ከቃልህ የተነሣ እውነተኛ ትሆናለህ፤ ባላጋራህንም በፍርድ ትረታለህ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ቢሆንም እግዚአብሔር እውነተኛ ነው።

5 ነገር ግን የእኛ ኃጢአት የእግዚአብሔርን ጽድቅ የሚያሳይ ከሆነ እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ስለ ኃጢአታችን ቢቀጣን ትክክለኛ ፈራጅ አይደለም ማለት ነውን? እዚህ ላይ የምናገረው እንደ ሰው አስተሳሰብ ነው።

6 ፈጽሞ አይደለም! እንዲህ ከሆነማ እግዚአብሔር በዓለም ላይ እንዴት ይፈርዳል?

7 ነገር ግን የእኔ ሐሰተኛነት የእግዚአብሔርን እውነት በመግለጥ፥ የክብሩን ብዛት የሚያሳይ ከሆነ ታዲያ፥ እኔ እንደ ኃጢአተኛ የሚፈረድብኝ ስለ ምንድን ነው?

8 አንዳንድ ሰዎች “መልካም ነገር እንድናገኝ ክፉ ነገር እናድርግ” እያልኩ የማስተምር አስመስለው ይከሱኛል፤ ስለዚህ እንዲህ ባሉት ላይ የሚፈረድባቸው ፍርድ ትክክለኛ ነው።


ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ መሆኑ

9 ታዲያ፥ እኛ አይሁድ ከአሕዛብ እንበልጣለን ማለት ነውን? ከቶ አይደለም! ሰዎች ሁሉ አይሁድም ሆኑ አሕዛብ ኃጢአተኞች መሆናቸውን ቀደም ብዬ አስረድቻለሁ።

10 እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፦ “አንድ እንኳ ጻድቅ ሰው የለም፤ አንድ እንኳን የለም፤

11 አስተዋይም የለም፤ እግዚአብሔርንም የሚፈልግ አንድም የለም።

12 ሁሉም ከመንገድ ወጥተዋል፤ በአንድነት ሆነው ተሳስተዋል። ደግ ሥራ የሚሠራ አንድ ሰው እንኳ የለም።

13 ሰውን የሚጐዳ ክፉ ቃል ለመናገር አፋቸው እንደ መቃብር የተከፈተ ነው፤ በምላሳቸው ያታልላሉ፤ የከንፈራቸውም ንግግር እንደ እባብ መርዝ የሚጐዳ ነው፤

14 አፋቸውም እርግማንና መራርነት ሞልቶበታል።

15 እግራቸው ሰውን ለመግደል የፈጠነ ነው፤

16 በመንገዳቸው የሚገኘው ጥፋትና ጒስቊልና ነው።

17 የሰላምን መንገድ አያውቁም፤

18 እግዚአብሔርን ከቶ አይፈሩም።”

19 የሕግ ትእዛዝ የሚመለከተው ከሕግ በታች ያሉትን እንደ ሆነ እናውቃለን፤ በዚህ ምክንያት ሰዎች የሚያመካኙት አጥተው ዝም ይላሉ፤ ዓለሙም ሁሉ በእግዚአብሔር ፍርድ ሥር ይሆናል።

20 ስለዚህ ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት፥ ሕግን በመፈጸም አይጸድቅም፤ ሕግ የሚያሳየው ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ መሆኑን ነው።


ጽድቅ በእምነት

21 አሁን ግን እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቅበት መንገድ ያለ ሕግ መሆኑ ተገልጦአል፤ ይህም በሙሴ ሕግና በነቢያት ተመስክሮአል።

22 ስለዚህ እግዚአብሔር ምንም ልዩነት ሳያደርግ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ ጽድቅን ይሰጣል።

23 ሰዎች ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋል፤ እግዚአብሔር የሰጣቸውንም ክብር አጥተዋል።

24 ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በፈጸመው በአዳኝነት ሥራ በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ይጸድቃሉ።

25 እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ በደሙ የኃጢአታቸውን ስርየት እንዲያገኙ ነው፤ እግዚአብሔር ይህን ማድረጉ በትዕግሥቱ የቀድሞውን ኃጢአት እንዳልነበረ በማድረግ የራሱን ትክክለኛ ፍርድ ለመግለጥ ነው።

26 በአሁኑም ዘመን እግዚአብሔር ራሱ ጻድቅ መሆኑን የሚያሳየው በኢየሱስ የሚያምኑትን ሁሉ በማጽደቅ ነው።

27 እንግዲህ የምንመካበት ነገር ምን አለ? በምንም አንመካም! የማንመካበትስ ምክንያት ምንድን ነው? ሕግን ስለምንፈጽም ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በእምነት ነው።

28 ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን የሚያጸድቀው፥ ሰው የሕግን ሥራ በመፈጸሙ ሳይሆን በእምነት መሆኑን እንገነዘባለን።

29 ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? በእርግጥ የአሕዛብም አምላክ ነው።

30 እግዚአብሔር አንድ ነው፤ አይሁድንም ሆነ አሕዛብን በእምነት የሚያጸድቅ እርሱ ነው።

31 ታዲያ፥ በእምነት ምክንያት ሕግን እንሽራለን ማለት ነውን? አይደለም፤ ይልቅስ ሕግን አጥብቀን እንይዛለን።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች