ሮሜ 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሰዎችን ማስደሰት እንደሚገባ 1 እኛ በእምነት ብርቱዎች የሆንን፥ የደካሞችን ድካም መሸከም ይገባናል እንጂ ራሳችንን ብቻ የምናስደስት መሆን የለብንም፤ 2 እያንዳንዳችን ሌላው ሰው በእምነቱ እንዲጠነክር እርሱን የሚጠቅመውንና የሚያስደስተውን ነገር እናድርግ። 3 ክርስቶስ ራሱን አላስደሰተም፤ ይልቁንም “ሰዎች አንተን የሰደቡበት ስድብ በእኔ ላይ ወረደ” የሚለው የቅዱሳት መጻሕፍት አባባል ደረሰበት። 4 ከቅዱሳት መጻሕፍት በምናገኛቸው ትዕግሥትና መጽናናት ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብለው የተጻፉት ሁሉ ትምህርት እንዲሆኑን ተጽፈዋል። 5 የትዕግሥትና የመጽናናት አምላክ እርስ በርሳችሁ የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል አብሮ የመኖርን ኅብረት ይስጣችሁ። 6 እንዲሁም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔር በአንድ ልብና በአንድ ቃል እንድታከብሩት ያድርጋችሁ። የወንጌል ቃል ለአሕዛብ እንደ ተሰበከ 7 ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ክብር እናንተን እንደ ተቀበላችሁ እናንተ ሁላችሁም አንዱ ሌላውን በደስታ ይቀበለው። 8 ይህንንም ስናገር እግዚአብሔር ለቀደሙት አባቶች የሰጠው ተስፋ እንዲፈጸምና የእግዚአብሔርም እውነተኛነት እንዲታወቅ ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ ሆነ ማለቴ ነው። 9 ክርስቶስ የአይሁድ አገልጋይ የሆነበትም ሌላው ምክንያት አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለ ምሕረቱ እንዲያመሰግኑት ነው፤ ይህም፦ “ስለዚህ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም በዝማሬ ምስጋና አቀርባለሁ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። 10 ደግሞም፥ “እናንተ አሕዛብ፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ደስ ይበላችሁ!” ተብሎ ተጽፎአል። 11 እንደገናም፦ “አሕዛብ ሁሉ! ጌታን አመስግኑት፤ ሕዝቦች ሁሉ አመስግኑት!” ተብሎ ተጽፎአል። 12 እንዲሁም ኢሳይያስ፦ “ከእሴይ ዘር የሚወለድ ይመጣል፤ የአሕዛብም መሪ ለመሆን ይነሣል፤ እነርሱም ተስፋቸውን በእርሱ ላይ ያደርጋሉ” ይላል። 13 ተስፋችሁ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል እያደገ እንዲሄድ የተስፋ አምላክ በእርሱ በመታመናችሁ ደስታንና ሰላምን በሙላት ይስጣችሁ። ጳውሎስ በድፍረት የጻፈበት ምክንያት 14 ወንድሞቼ ሆይ! በደግነት የተሞላችሁ፥ በዕውቀት የበለጸጋችሁና እያንዳንዳችሁም ሌላውን ለመምከር የምትችሉ መሆናችሁን ተረድቼአለሁ። 15 አንዳንድ ነገሮችን ላስታውሳችሁ ፈልጌ ይህን መልእክት እግዚአብሔር በሰጠኝ ጸጋ መሠረት በድፍረት ጻፍኩላችሁ። 16 ይህም ጸጋ የተሰጠኝ የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል ለአሕዛብ በማብሠር እንደ ካህን ሆኜ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ስለዚህ አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሰና እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት ሆነው እንዲቀርቡ አገለግላለሁ። 17 በዚህ ምክንያት በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን ለማገልገል በመቻሌ እመካለሁ። 18 አሕዛብ ታዛዦች እንዲሆኑ ለማድረግ ክርስቶስ በእኔ ቃልና ሥራ አማካይነት የሠራው ነገር ካልሆነ በቀር ምንም ነገር ለመናገር አልደፍርም። 19 እንዲሁም በታላላቅ ተአምራትና በድንቅ ሥራዎች፥ በመንፈስ ቅዱስም ኀይል ከኢየሩሳሌምና ከአካባቢዋ ጀምሮ እስከ እልዋሪቆን ድረስ የክርስቶስን ወንጌል አስተምሬአለሁ። 20 የዘወትር ምኞቴም ሌላው ሰው በጣለው መሠረት ላይ መገንባት ሳይሆን የክርስቶስ ስም ባልተሰማበት ስፍራ ሁሉ መልካሙን ዜና ማብሠር ነው። 21 ይህም፦ “ከዚህ በፊት ስለ እርሱ ምንም ያልተነገራቸው ሰዎች ያያሉ፤ ስለ እርሱ ያልሰሙም ያስተውላሉ” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ጳውሎስ ወደ ሮም ለመሄድ እንደ ዐቀደ 22 እስከ አሁን ወደ እናንተ ለመምጣት ያልቻልኩት ቀደም ብዬ በተናገርኩት ምክንያት ነው። 23 አሁን ግን በዚህ አካባቢ ባሉት አገሮች የምሠራባቸው ቦታዎች ስለሌሉ፥ እንዲሁም ከብዙ ዓመቶች ጀምሬም እናንተን ለመጐብኘት ከፍ ያለ ምኞት ስላለኝ 24 ወደ እስፔን በምሄድበት ጊዜ እግረ መንገዴን ልጐበኛችሁ ዐቅጃለሁ። ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ደስ ብሎኝ ከቈየሁ በኋላ ጒዞዬን ለመቀጠል የሚያስችለኝን ርዳታ እንደምታደርጉልኝ ተስፋ አደርጋለሁ። 25 አሁን ግን ለእግዚአብሔር ወገኖች የሚሰጥ የገንዘብ ርዳታ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ። 26 ይኸውም የመቄዶንያና በአካይያ የሚገኙ የእግዚአብሔር ወገኖች በኢየሩሳሌም ላሉት ድኾች የገንዘብ ርዳታ ለመላክ በፈቃዳቸው ስለ ወሰኑ ነው። 27 ይህንንም ርዳታ በፈቃደኛነት የለገሡት ግዴታቸው በመሆኑ ነው፤ አሕዛብ ከአይሁድ ጋር የመንፈስ በረከት ተካፋዮች ከሆኑ እነርሱም በሥጋዊ በረከታቸው አይሁድን የመርዳት ግዴታ አለባቸው። 28 ስለዚህ ይህን የተሰበሰበውን የገንዘብ ርዳታ ወደ ኢየሩሳሌም ወስጄ የማስረከብ ሥራዬን ከፈጸምኩ በኋላ በእናንተ በኩል አድርጌ ወደ እስፔን እሄዳለሁ። 29 ወደ እናንተ በምመጣበት ጊዜም የክርስቶስን በረከት በሙላት ይዤላችሁ እንደምመጣ ዐውቃለሁ። 30 ወንድሞቼ ሆይ! ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ በትግሌ እንድትረዱኝ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ ፍቅር እለምናችኋለሁ። 31 የምትጸልዩልኝም በይሁዳ ምድር ካሉት ከማያምኑ ሰዎች እጅ እንድድንና በኢየሩሳሌም ያለኝ አገልግሎትም በእግዚአብሔር ወገኖች ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ነው። 32 ይህም ከሆነ በኋላ የእግዚአብሔር ፈቃድ ቢሆን በደስታ ወደ እናንተ መጥቼ ከእናንተ ጋር ማረፍ እወዳለሁ። 33 የሰላም አምላክ ከሁላችሁም ጋር ይሁን! አሜን። |