Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሮሜ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ለመንግሥት ባለሥልጣኖች መታዘዝ እንደሚገባ

1 ማንኛውም ሥልጣን የሚገኘው በእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነና አሁን ያሉትም ባለሥልጣኖች የተሾሙት በእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ ሰው ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣን መታዘዝ አለበት።

2 ስለዚህ ባለሥልጣንን የሚቃወም ሁሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይቃወማል፤ የማይታዘዝም ሁሉ በራሱ ላይ የቅጣትን ፍርድ ያመጣል።

3 ገዢዎች የሚያስፈሩት ክፉ አድራጊዎችን እንጂ መልካም አድራጊዎችን አይደለም፤ ባለሥልጣንን እንዳትፈራ ትፈልጋለህን? እንግዲያውስ መልካሙን ነገር አድርግ፤ ከእርሱም ምስጋናን ታገኛለህ።

4 ባለሥልጣን ለአንተ መልካም እንዲያደርግ የተሾመ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፤ ባለሥልጣን ሰይፍ የታጠቀው በከንቱ ስላልሆነ ክፉ አድራጊ ከሆንክ ባለሥልጣንን ፍራ፤ እርሱ ክፉ አድራጊዎችን በመቅጣትና የእግዚአብሔርን በቀል በማሳየት እግዚአብሔርን ያገለግላል።

5 ስለዚህ ለመንግሥት ባለሥልጣኖች መታዘዝ ይገባችኋል፤ የምትታዘዙትም የእግዚአብሔርን ቊጣ ስለ መፍራታችሁ ብቻ ሳይሆን ኅሊናችሁም ስለሚወቅሳችሁ መሆን አለበት።

6 ግብር የምትከፍሉትም ስለዚህ ነው፤ ባለሥልጣኖች በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩት እግዚአብሔርን ለማገልገል ነው።

7 እንግዲህ ለበላይ ባለሥልጣን ሊደረግ የሚገባውን ሁሉ አድርጉ፤ ግብር ለሚገባው ግብርን፥ ቀረጥ ለሚገባው ቀረጥን ክፈሉ፤ መፈራት ለሚገባው መፈራትን፥ ክብር ለሚገባው ክብርን ስጡ።


እርስ በርስ ስለ መፈቃቀር

8 የማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤ ሊኖርባችሁ የሚገባ ዕዳ እርስ በርስ መዋደድ ብቻ ይሁን፤ ሰውን የሚወድ ሕግን ይፈጽማል።

9 “አታመንዝር፤ አትግደል፤ አትስረቅ፤ የሌላ ሰው የሆነውን ማናቸውንም ነገር አትመኝ” የሚሉት ትእዛዞችና ሌሎችም ትእዛዞች ሁሉ “ሰውን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ” በሚለው በአንዱ ትእዛዝ ተጠቃለው ይገኛሉ።

10 ሰውን የሚወድ ሁሉ በሚወደው ላይ ክፉ ነገር አያደርግበትም፤ ስለዚህ ሰውን የሚወድ ሕግን ሁሉ ይፈጽማል ማለት ነው።

11 እንግዲህ ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት አሁን መድረሱን ዕወቁ፤ በፊት ካመንበት ጊዜ ይልቅ አሁን የምንድንበት ቀን ይበልጥ ወደ እኛ ቀርቦአል።

12 ሌሊቱ እያለፈ ነው፤ ቀኑም ቀርቦአል፤ ስለዚህ በጨለማ የሚሠራውን ሥራ እንተው፤ የብርሃንን የጦር መሣሪያ እንልበስ።

13 ቅጥ ባጣ ፈንጠዝያ፥ በስካር፥ በዝሙትና በመዳራት፥ በጭቅጭቅና በምቀኝነት ሳይሆን በቀን ብርሃን እንደሚኖሩ ሰዎች በጨዋነት እንመላለስ።

14 ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት እንጂ የሥጋችሁን ፍላጎት ለማርካት አታስቡ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች