Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

ሮሜ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ጨርሶ ያልጣለ መሆኑ

1 እስቲ ደግሞ ልጠይቅ፦ እግዚአብሔር የራሱን ሕዝብ ጥሎአልን? ከቶ አልጣለውም! እኔም ራሴ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከአብርሃም ዘር የሆንኩ የብንያም ነገድ ነኝ።

2 እግዚአብሔር አስቀድሞ የመረጠውን ሕዝብ አልጣለውም፤ ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ኤልያስ ምን እንዳለ አታስታውሱምን? ደግሞስ ኤልያስ የእስራኤልን ሕዝብ በእግዚአብሔር ፊት ምን ብሎ እንደ ከሰሰ አታውቁምን?

3 በዚያን ጊዜ ኤልያስ “ጌታ ሆይ! ነቢያትህን ገደሉ፤ መሠዊያዎችህን አፈረሱ፤ እኔ ብቻ ቀረሁ፤ እኔንም ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ” ብሎ ነበር።

4 ነገር ግን እግዚአብሔር ምን ብሎ መለሰለት? “ባዓል ለተባለው ጣዖት ያልሰገዱትን ሰባት ሺህ ሰዎች ለራሴ አስቀርቻለሁ” ብሎታል።

5 በአሁኑም ዘመን ቢሆን፥ በጸጋ ተመርጠው የቀሩ ጥቂት እስራኤላውያን አሉ።

6 ምርጫው በጸጋ ከሆነ በሥራ አይደለም ማለት ነው፤ በሥራ ከሆነማ፥ ጸጋ ዋጋቢስ በሆነ ነበር።

7 ታዲያ፥ ውጤቱ ምን ሆነ? እስራኤላውያን የፈለጉትን አላገኙም፤ የተመረጡት ግን የፈለጉትን አገኙ፤ የቀሩት ልባቸውን አደነደኑ።

8 ይህም “እግዚአብሔር ልቡናቸውን አደነዘዘ፤ ስለዚህ እስከ ዛሬ ድረስ በዐይናቸው አያዩም፤ በጆሮአቸውም አይሰሙም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው።

9 ዳዊትም፦ “ማእዳቸው የሚይዝ ወጥመድ፥ የሚጥል ጒድጓድ ሆኖ ያሠቃያቸው! ያደረጉት ክፋት በራሳቸው ላይ ይድረስ!

10 ዐይናቸው እንዳያይ ይጨልም፤ ወገባቸውም በችግር ሁልጊዜ ይጒበጥ” ብሎአል።

11 እስቲ፥ እንደገና ልጠይቅ፤ አይሁድ የወደቁት ዳግመኛ እንደማይነሡ ሆነው ነውን? አይደለም! በአይሁድ በደል ምክንያት አሕዛብ መዳንን አገኙ፤ ይህም የሆነው አይሁድ በአሕዛብ እንዲቀኑ ለማድረግ ነው።

12 የአይሁድ በደል ለዓለም ብዙ በረከት አስገኝቶአል፤ የእነርሱም ውድቀት ለአሕዛብ በረከት ሆኖአል፤ አይሁድ ቢድኑማ ኖሮ በረከቱ ምን ያኽል ብዙ በሆነ ነበር!


የአሕዛብ መዳን

13 አሁን እንግዲህ የምናገረው ለእናንተ ለአሕዛብ ነው፤ የአሕዛብም ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን በአገልግሎቴ ክብር ይሰማኛል፤

14 ይህንንም ማድረጌ የሥጋ ዘመዶቼ የሆኑትን አይሁድ ለማስቀናት ነው፤ በዚህም ሁኔታ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዶቹን ለማዳን እችል ይሆናል በማለት ነው።

15 እግዚአብሔር እነርሱን በጣላቸው ጊዜ ሌላው የዓለም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቀ እግዚአብሔር እነርሱን በሚቀበላቸው ጊዜ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ይህማ ከሞት እንደ መነሣት ያኽል ነው!

16 ከአንድ ዐይነት ሊጥ የመጀመሪያው ክፍል የተቀደሰ ከሆነ ሊጡ በሙሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ እንዲሁም የአንድ ዛፍ ሥሩ የተቀደሰ ከሆነ ቅርንጫፎቹም የተቀደሱ ይሆናሉ።

17 እንደ ጓሮ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆኑ አይሁድ ተቈርጠው ቢወድቁና እናንተ እንደ ዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆናችሁ አሕዛብ በቦታቸው ተተክታችሁ የእነርሱን ሀብትና በረከት ተካፋዮች ብትሆኑ፥

18 እናንተ አሕዛብ እንደ ቅርንጫፍ ተቈርጠው በወደቁት አይሁድ ላይ አትታበዩ፤ ብትታበዩ ግን እናንተ ቅርንጫፎች ብቻ በመሆናችሁ ሥሩ እናንተን ይሸከማችኋል እንጂ እናንተ ሥሩን የማትሸከሙ መሆናችሁን አስታውሱ።

19 ነገር ግን “ቅርንጫፎች ተሰብረው የወደቁት እኔ በቦታቸው እንድተካ ነው” ትሉ ይሆናል።

20 አባባላችሁስ ልክ ነው፤ ነገር ግን እነርሱ ተቈርጠው የወደቁት ባለማመናቸው ሲሆን እናንተ ጸንታችሁ የቆማችሁት በማመናችሁ ነው፤ ታዲያ፥ መፍራት እንጂ መታበይ አይገባችሁም።

21 እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት አይሁድ ካልራራላቸው ለእናንተም አይራራላችሁም።

22 እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና አስፈሪነት ተመልከቱ፤ አስፈሪነቱን የሚያሳየው በወደቁት ላይ ሲሆን ቸርነቱን የሚያሳየው ግን ለእናንተ ነው፤ ይህንንም የሚያደርገው እርሱን በማመን ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው፤ ባትጸኑ ግን እናንተም ተቈርጣችሁ ትወድቃላችሁ።

23 አይሁድ አለማመናቸውን ቢያስወግዱ ወደ ቀድሞው ቦታቸው ይመለሳሉ፤ እግዚአብሔር ወደ ቀድሞው ቦታቸው ሊመልሳቸው ይችላል።

24 እናንተ አሕዛብ ግን በተፈጥሮ የዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ሆናችሁ ሳለ ያለ ቦታችሁ በጓሮ የወይራ ዛፍ ላይ መተከል ከቻላችሁ እነዚህ በተፈጥሮአቸው የጓሮ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች የሆኑት አይሁድማ ወደ ቀድሞው ቦታቸው ተመልሰው መተከል እንዴት አይቻላቸውም!


የእግዚአብሔር ምሕረት ለሁሉም መሆኑ

25 ወንድሞቼ ሆይ! “ዐዋቂዎች ነን” ብላችሁ አትመኩ፤ የምነግራችሁ አንድ ምሥጢር አለ፤ ይኸውም የእስራኤላውያን እምቢተኛነት ለዘለቄታው ሳይሆን አሕዛብ ሁሉ በሙላት ወደ እግዚአብሔር እስኪመጡ ድረስ መሆኑን ነው።

26 እንግዲህ በዚህ ዐይነት እስራኤላውያን ሁሉ ይድናሉ። ስለዚህም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፦ “አዳኝ ከጽዮን ይመጣል፤ ከያዕቆብም ዘር ሁሉ ክፋትን ያስወግዳል፤

27 ኃጢአታቸውንም በደመሰስኩላቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው።”

28 እስራኤላውያን የወንጌልን ቃል ባለመቀበላቸው ስለ እናንተ ስለ አሕዛብ ጥቅም የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነዋል፤ ነገር ግን በምርጫ በኩል በነገድ አባቶች ምክንያት የእግዚአብሔር ወዳጆች ናቸው።

29 እግዚአብሔር ከመረጠና ጸጋውን ከሰጠ በኋላ ባደረገው ነገር ሐሳቡን አይለውጥም።

30 እናንተ አሕዛብ ቀድሞ ለእግዚአብሔር የማትታዘዙ ነበራችሁ፤ አሁን ግን አይሁድ ባለመታዘዛቸው ምክንያት እናንተ የእግዚአብሔርን ምሕረት አገኛችሁ።

31 እናንተ ምሕረትን ባገኛችሁበት ዐይነት እነርሱም ምሕረትን እንዲያገኙ እነርሱ አሁን ለእግዚአብሔር የማይታዘዙ ሆነዋል።

32 እግዚአብሔር ምሕረቱን ለሰው ሁሉ ለማሳየት ሲል ሰዎችን ሁሉ የእምቢተኛነታቸው እስረኞች እንዲሆኑ አደረጋቸው።


ለእግዚአብሔር የቀረበ ምስጋና

33 የእግዚአብሔር ባለጸግነትና ጥበብ ዕውቀትም እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ የማይመረመር፥ መንገዱም የማይታወቅ ነው።

34 “የጌታን አሳብ የሚያውቅ ማነው? የእርሱ አማካሪ የሚሆንስ ማነው?

35 ለእግዚአብሔር የሚያበድርና ያበደረውንም የሚወስድ ማነው?”

36 ሁሉም ነገር የተገኘው ከእርሱ፥ በእርሱና ለእርሱ ነው፤ ለዘለዓለም ክብር ለእርሱ ይሁን! አሜን!

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች