Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 90 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔርና ሰው

1 እግዚአብሔር ሆይ! በዘመናት ሁሉ አንተ መጠጊያችን ነህ።

2 ተራራዎችን ከመሥራትህና ዓለምንም ከመፍጠርህ በፊት፥ አንተ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም አምላክ ነህ።

3 ሰው ወደነበረበት እንዲመለስ ታዛለህ፤ ተመልሶም ትቢያ እንዲሆን ታደርገዋለህ።

4 ለአንተ አንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነው፤ አልፎ እንደ ሄደው እንደ ትናንት ነው፤ እንደ ሌሊትም ጥቂት ሰዓቶች ነው።

5 ሕይወታችንን ልክ እንደ ሕልም ታሳልፈዋለህ፤ እኛ በየማለዳው እንደሚታደስ የሣር ቡቃያ ነን።

6 ሣር ወዲያው አድጎ ያብባል፤ ሲመሽ ግን ጠውልጎ ይደርቃል።

7 እኛ በቊጣህ ጠፍተናል፤ በመዓትህም ደንግጠናል።

8 ኃጢአታችንን በፊትህ ታኖራለህ፤ የተሰወረውንም በደላችንን ለአንተ በሚታይ ቦታ ታስቀምጣለህ።

9 ዘመናችን ሁሉ በቊጣህ ያልፋሉ የዕድሜአችንም ፍጻሜ እንደ እስትንፋስ ነው።

10 ዕድሜአችን ሰባ ዓመት ነው፤ ቢበዛም ሰማኒያ ዓመት ነው፤ እነዚያም ዘመናት በችግርና በሐዘን የተሞሉ ናቸው፤ ዕድሜአችን በቶሎ ያልቃል፤ እኛም እናልፋለን።

11 አንተን የሚፈሩ ሰዎች ቊጣህን የሚረዱትን ያኽል፥ የአንተን የቊጣ ኀይል የሚያውቅ ማነው?

12 ጥበበኞች ለመሆን እንድንችል ዕድሜአችን ምን ያኽል አጭር እንደ ሆነ አስተምረን።

13 እግዚአብሔር ሆይ! ቊጣህ እስከ መቼ ይቈያል? እባክህ ለአገልጋዮችህ ራራ!

14 በዘመናችን ሁሉ እንድንዘምርና ደስ እንዲለን ዘለዓለማዊውን ፍቅርህን በየማለዳው አሳየን።

15 የመከራ ዓመቶች አሳልፈናል፤ ብዙ ሐዘንም ደርሶብናል፤ በዚህ ሁሉ ልክ ደስታን ስጠን።

16 እኛ አገልጋዮችህ ታላቁን ሥራህን እንድናይ ፍቀድልን። ልጆቻችንም የኀይልህን ክብር እንዲያዩ አድርጋቸው።

17 እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ! በረከትህ ከእኛ ጋር ይሁን፤ የምናደርገውንም ሁሉ አሳካልን።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች