Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 88 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእግዚአብሔርን ርዳታ ለማግኘት የቀረበ ልመና

1 አዳኜ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! ትረዳኝ ዘንድ በቀን ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ ሌሊቱንም በአንተ ፊት አለቅሳለሁ።

2 እባክህ ጸሎቴን ስማ! ጩኸቴንም አድምጥ!

3 ብዙ መከራ ስለ ደረሰብኝ ለመሞት ተቃርቤአለሁ።

4 ሞተው ወደ መቃብር ከሚወርዱት ሰዎች ጋር ተቈጥሬአለሁ፤ ምንም ረዳት እንደሌለው ሰው ሆኜአለሁ።

5 በሙታን መካከል ፈጽሞ እንደ ተተዉ፥ ተገድለው በመቃብር እንደ ተጋደሙ፥ ከእንግዲህ ፈጽሞ እንደማታስታውሳቸውና የአንተ እንክብካቤ ከእነርሱ እንደ ተቋረጠ ሰዎች መስዬአለሁ።

6 አንተ ወደ መቃብር አዘቅት ወደ ጨለመውና ጥልቅ ወደ ሆነው ጒድጓድ አወረድከኝ።

7 ቊጣህ እጅግ ከብዶኛል፤ የቊጣህም ማዕበል አጥለቅልቆኛል።

8 ወዳጆቼ ሁሉ ከእኔ እንዲርቁ አደረግህ፤ በፊታቸውም አጸያፊ አደረግኸኝ፤ ዙሪያዬ ታጥሮአል፤ ማምለጫም የለኝም።

9 ሐዘኔ ከመብዛቱ የተነሣ ዐይኖቼ ደከሙ፤ እግዚአብሔር ሆይ! በየቀኑ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ እጆቼንም ለጸሎት ወደ አንተ እዘረጋለሁ።

10 ለሙታን ተአምራትን ታደርጋለህን? እነርሱስ ተነሥተው ያመሰግኑሃልን?

11 ዘለዓለማዊ ፍቅርህ በመቃብር፥ ታማኝነትህ በጥፋት ቦታ ይነገራልን?

12 ተአምራትህ በጨለማ ስፍራ ይታወቃሉን? ታዳጊነትህስ በተረሱ ሰዎች አገር ይታያልን?

13 እግዚአብሔር ሆይ! እንድትረዳኝ ወደ አንተ እጮኻለሁ፤ በየማለዳውም ወደ አንተ እጸልያለሁ።

14 እግዚአብሔር ሆይ! ለምን ትጥለኛለህ? ፊትህንስ ከእኔ ለምን ትሰውራለህ?

15 ከልጅነቴ ጀምሮ ጭንቀት ደርሶብኝ እስከ ሞት ተቃርቤአለሁ፤ ከማስደንገጥህ የተነሣ ተስፋ ቈርጬአለሁ።

16 ብርቱ ቊጣህ አደቀቀኝ፤ አስፈሪው ቅጣትህ ያጠፋኛል።

17 እነርሱ ቀኑን ሙሉ እንደ ጐርፍ ከበቡኝ፤ ፈጽመውም አሰጠሙኝ።

18 የቅርብ ወዳጆቼንና ጓደኞቼን ከእኔ አርቀህ ጨለማ ብቻ ከእኔ ጋር እንዲቀር አደረግህ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች