መዝሙር 82 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ከሁሉ በላይ ነው 1 እግዚአብሔር በሰማያዊው ጉባኤ አማልክት ሁሉ በተሰበሰቡ ጊዜ፥ በመካከላቸው ተገኝቶ ፍርድ ይሰጣል፦ 2 “እስከ መቼ ትክክል ያልሆነ ፍርድ ትፈርዳላችሁ? እስከ መቼ ለክፉዎች ታዳላላችሁ? 3 ለደካሞችና ለሙት ልጆች በትክክል ፍረዱ፤ የድኾችንና የተጨቈኑትን ሰዎች መብት ጠብቁ። 4 ደካሞችንና ችግረኞችን አድኑ፤ ከክፉዎችም ጥቃት አስጥሉአቸው። 5 “እነርሱ ግን ምንም አያውቁም፤ አይገባቸውምም፤ በጨለማ ይመላለሳሉ፤ በዚህም ጊዜ የምድር መሠረትዋ እየተናወጠ ነው። 6 ‘እናንተ አማልክት ናችሁ፤ ሁላችሁም የልዑል እግዚአብሔር ልጆች ናችሁ’ አልኩ። 7 ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ፤ የሕይወታችሁም ፍጻሜ እንደ ማንኛውም ምድራዊ ገዢ ነው።” 8 አምላክ ሆይ! ተነሥ! መንግሥታት ሁሉ ያንተ ስለ ሆኑ ለዓለም ፍርድን ስጥ። |