Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የመማጠኛ ጸሎት

1 እግዚአብሔር ሆይ! ቃሌን አድምጥ፤ መቃተቴንም ስማ።

2 ንጉሤና አምላኬ ሆይ! ወደ አንተ ስለምጸልይ ለእርዳታ የምጮኸውን ጩኸት አድምጥ።

3 እግዚአብሔር ሆይ! ልመናዬን ወደ አንተ አቅርቤ መልስህን ስጠብቅ በየማለዳው ጸሎቴን ስማ።

4 አንተ በኃጢአት የምትደሰት አምላክ አይደለህም፤ ክፉዎችም ከአንተ ጋር አይኖሩም።

5 ትዕቢተኞች በፊትህ አይቆሙም፤ ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ትጠላለህ።

6 ሐሰት የሚናገሩትን ሁሉ ታጠፋለህ፤ ነፍሰ ገዳዮችንና አታላዮችን ትጸየፋለህ።

7 እኔ ግን በታላቅ ምሕረትህ ወደ ቤትህ እገባለሁ፤ ወደ ቤተ መቅደስህ በአክብሮት እሰግዳለሁ።

8 እግዚአብሔር ሆይ! የሚጠባበቁኝ ጠላቶቼ ብዙዎች ናቸው! ስለዚህ ፈቃድህን እንዳደርግ ምራኝ፤ መንገድህንም በፊቴ አቅናልኝ።

9 ጠላቶቼ የሚናገሩት ሁሉ ከእውነት የራቀ ስለ ሆነ፥ ከአፋቸው እውነት አይገኝም፤ ሐሳባቸውም በተንኰል የተሞላ ነው፤ ጒሮሮአቸውም እንደ ተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸውም ሰውን ይሸነግላሉ።

10 አምላክ ሆይ! ፍረድባቸው፤ የራሳቸው ሤራ መውደቂያቸው ይሁን፤ በአንተ ላይ ስለ ዐመፁ ስለ ብዙ በደላቸው አስወግዳቸው፤

11 በአንተ ከለላ ሥር ያሉ ሁሉ ይደሰቱ፤ ለዘለዓለምም እልል ይበሉ የአንተን ስም የሚወዱትን ሁሉ በደስታም እንዲፈነድቁ ከልላቸው።

12 እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ጻድቃንን ትባርካለህ፤ በቸርነትህም እንደ ጋሻ መከላከያ ትሆንላቸዋለህ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች