Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 46 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው

1 እግዚአብሔር መጠጊያችንና ኀይላችን ነው፤ ችግር በሚደርስብን ጊዜ ሁሉ ረዳታችን ነው።

2 ስለዚህ ምድር ብትናወጥ፥ ተራራዎች ወደ ጥልቅ ባሕር ቢወድቁ፥

3 ባሕሮች ታውከው ድምፃቸውን ቢያሰሙ፥ በእነርሱም የእንቅስቃሴ ኀይል ተራራዎች ቢንቀጠቀጡ አንፈራም።

4 ጅረቶችዋ የልዑል እግዚአብሔርን ቅዱስ ማደሪያ፥ የአምላክን ከተማ የሚያስደስቱ አንዲት ወንዝ አለች።

5 እግዚአብሔር ከእርስዋ ጋር ስለ ሆነ ያቺ ከተማ አትናወጥም፤ ጠዋት በማለዳ እግዚአብሔር ይረዳታል።

6 ሕዝቦች ተሸበሩ፤ ነገሥታትም ወደቁ፤ እግዚአብሔር ድምፁን ባሰማ ጊዜ ምድር ቀለጠች።

7 የሠራዊት አምላክ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።

8 ኑ፥ የእግዚአብሔርን ሥራ እዩ፤ በምድር ላይ ያመጣውን ጥፋት ተመልከቱ።

9 እርሱ በመላው ዓለም የሚካሄደውን ጦርነት ሁሉ ያቆማል፤ ቀስትንና ጦርን ይሰብራል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል።

10 ጸጥ ብላችሁ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ዕወቁ፤ በሕዝቦች መካከል ከፍ ከፍ እላለሁ፤ በምድርም ላይ ከፍ ከፍ እላለሁ።

11 የሠራዊት አምላክ ከእኛ ጋር ነው፤ የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች