Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ እግዚአብሔር ቸርነት የሚቀርብ ምስጋና

1 ዘወትር እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ምስጋናውም ዘወትር በአንደበቴ ነው።

2 በሙሉ ልቤ በእግዚአብሔር እመካለሁ፤ ትሑቶች ይህን ሰምተው ደስ ይበላቸው!

3 የእግዚአብሔርን ታላቅነት ከእኔ ጋር አስታውቁ፤ በኅብረትም ስሙን እናክብር።

4 የእግዚአብሔርን ርዳታ ፈለግኹ እርሱም ሰማኝ፤ ከምፈራውም ነገር ሁሉ አዳነኝ።

5 ወደ እርሱ የሚመለከቱ ሁሉ ፊታቸው ይበራል፤ ፊታቸውም ከቶ በኀፍረት አይሸፈነም።

6 ይህ ድኻ ሰው ተጣራ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤ ከችግሩም ሁሉ አዳነው።

7 የእግዚአብሔር መልአክ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን ሰዎች ይጠብቃል፤ በዙሪያቸውም ሆኖ ከአደጋ ያድናቸዋል።

8 የእግዚአብሔርን ደግነት እዩና ቅመሱ፤ እርሱን ከለላ ያደረገ የተባረከ ነው።

9 እርሱን የሚፈሩት ሁሉ ምንም ስለማያጡ እናንተ ቅዱሳኑ እግዚአብሔርን ፍሩ

10 የአንበሳ ደቦሎች ያጣሉ፤ ይራባሉም፤ እግዚአብሔርን የሚፈልጉት ግን ምንም አይጐድልባቸውም፤ መልካም ነገርም አያጡም።

11 ልጆቼ ሆይ! ኑ አድምጡኝ፤ እኔም እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ።

12 ከእናንተ መኖርንና ለብዙ ዘመንም መልካም ነገርን ለማየት የሚመኝ ማነው?

13 እንግዲያውስ መጥፎ ነገር ከማውራትና ሐሰት ከመናገር ተቈጠቡ።

14 ከክፉ ነገር ሽሹ፤ መልካም ነገርንም አድርጉ፤ ሰላምን ፈልጉአት፤ ተከተሉአትም።

15 እግዚአብሔር ወደ ጻድቃን ይመለከታል፤ ጸሎታቸውንም ያደምጣል።

16 ክፉ አድራጊዎችን ግን ይቃወማል፤ መታሰቢያቸውንም ከምድር ላይ ያጠፋል።

17 ጻድቃን ወደ እግዚአብሔር ይጮኻሉ፤ እርሱም ይሰማቸዋል፤ ከችግራቸውም ሁሉ ያድናቸዋል።

18 ልባቸው ለተሰበረ እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የደቀቀውንም ያድናቸዋል።

19 ጻድቅ ብዙ መከራ ይደርስበታል፤ እግዚአብሔር ግን ከዚህ ሁሉ ያድነዋል።

20 እግዚአብሔር አጥንቶቹን ስለሚጠብቅ ከእነርሱ አንዱ እንኳ አይሰበርም።

21 ክፋት ክፉ ሰዎችን ይገድላል፤ ደጋግ ሰዎችን የሚጠሉ ሁሉ ይቀጣሉ።

22 እግዚአብሔር የአገልጋዮቹን ሕይወት ያድናል፤ በእርሱ የተማጠኑትም ክፉ ነገር አይደርስባቸውም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች