Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእግዚአብሔርን መሪነትና ጠባቂነት ለማግኘት የቀረበ ጸሎት

1 እግዚአብሔር ሆይ! የልቤን ሐሳብ ወደ አንተ አቀርባለሁ።

2 አምላኬ ሆይ! በአንተ እታመናለሁ፤ ጠላቶቼ ድል እንዲቀዳጁ አድርገህ አታሳፍረኝ።

3 በአንተ የሚታመኑት ኀፍረት አይደርስባቸውም፤ ኀፍረት የሚደርስባቸው፥ በአንተ ላይ ለማመፅ የሚጣደፉት ናቸው።

4 አምላክ ሆይ! ዱካህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ።

5 አንተ የምታድነኝ አምላኬ ነህና እውነትህን ተከትዬ እንድኖር አስተምረኝ፤ እኔ ዘወትር የምታመነው በአንተ ነው።

6 እግዚአብሔር ሆይ! ከጥንት ጀምሮ የምታሳየውን ምሕረትና ዘለዓለማዊ ፍቅር አስብ።

7 አምላክ ሆይ! እንደ ቸርነትህ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ አስበኝ እንጂ የወጣትነት ኃጢአቴን ወይም በደሌን አታስብብኝ!

8 እግዚአብሔር ደግና ቀጥተኛ ስለ ሆነ፥ ሊከተሉት የሚገባቸውን መንገድ ለኃጢአተኞች ያስተምራል።

9 ትሑቶችንም በትክክለኛው መንገድ ይመራቸዋል፤ መንገዱንም ያስተምራቸዋል።

10 የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ትእዛዞች ለሚጠብቁ ሰዎች የእግዚአብሔር መንገዶች ሁሉ ፍቅርና ታማኝነት ናቸው።

11 እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ስምህ ክብር እጅግ የበዛውን ኃጢአቴን ይቅር በልልኝ።

12 እግዚአብሔርን የሚፈሩ እነማን ናቸው? እነርሱ መከተል የሚገባቸውን አካሄድ እንዲመርጡ እርሱ ያስተምራቸዋል።

13 ዘወትር በብልጽግና ይኖራሉ፤ ልጆቻቸውም ምድርን ይወርሳሉ።

14 እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሁሉ ወዳጃቸው ነው፤ ለእነርሱ የገባውንም ቃል ኪዳን ያጸናል።

15 ከወጥመዶች ሁሉ ስለሚያድነኝ ሁልጊዜ ወደ እርሱ እመለከታለሁ።

16 እኔ ብቸኛና ችግረኛ ስለ ሆንኩ አምላክ ሆይ! ወደ እኔ ተመለስ፤ በጎነትንም አድርግልኝ።

17 ከደረሰብኝ ችግር ሁሉ እንድላቀቅ አድርገኝ፤ ከጭንቀቴም ሁሉ አድነኝ።

18 ችግሬንና ሥቃዬን ተመልከት፤ ኃጢአቴንም ሁሉ ይቅር በልልኝ።

19 ጠላቶቼ ምን ያኽል እንደ በዙ እይ፤ ምን ያኽል እንደ ጠሉኝም ተመልከት።

20 ጠብቀኝ፤ አድነኝም፤ አንተን መጠጊያ ስላደረግሁ ኀፍረት እንዲደርስብኝ አታድርግ።

21 አምላክ ሆይ! አንተን ተስፋ አደርጋለሁ፤ ቅንነትና ቀጥተኛነት እንዲጠብቁኝ አድርግ።

22 አምላክ ሆይ! እስራኤልን ከመከራው ሁሉ አድን!

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች