መዝሙር 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ተገኘው ድል የቀረበ ምስጋና 1 አምላክ ሆይ! ኀይልን ስለ ሰጠኸው ንጉሥ ደስ ብሎታል፤ ድልን ስለ አቀዳጀኸውም ሐሴት ያደርጋል። 2 የልቡን ምኞት ሰጥተኸዋል፤ የለመነህንም አልከለከልከውም። 3 በብዙ በረከትን ሰጥተህ ተቀበልከው፤ በራሱ ላይ የንጹሕ ወርቅ ዘውድ ደፋህለት። 4 ሕይወትን እንድትሰጠው ለመነህ፤ አንተም ረጅም ዕድሜና ዘለዓለማዊ የሆነ ሕይወትን ሰጠኸው። 5 አንተ በሰጠኸው ድሎች ምክንያት ታላቅ ክብር አገኘ፤ ክብርንና ግርማን አቀዳጀኸው። 6 የዘለዓለም በረከትን ሰጠኸው፤ አንተም ከእርሱ ጋር በመገኘትህ ደስ ታሰኘዋለህ፤ 7 ንጉሡ የሚተማመነው በእግዚአብሔር ነው፤ የማያቋርጠው የልዑል እግዚአብሔር ፍቅር ከእርሱ ጋር ስለ ሆነም አይናወጥም። 8 እጅህ ጠላቶችህን ሁሉ፥ ቀኝ እጅህም የሚጠሉህን ሁሉ ያገኛል። 9 በምትገለጥበት ጊዜ ከምድጃ እንደሚወጣ የእሳት ነበልባል ታቃጥላቸዋለህ፤ እግዚአብሔር በቊጣው ወላፈን ይለበልባቸዋል፤ እሳትም ይበላቸዋል። 10 ትውልዳቸውን ከምድር ላይ ታጠፋለህ፤ ዘራቸውንም ከሕዝቦች መካከል ለይተህ ትደመስሳለህ። 11 በአንተ ላይ ክፉ ነገር ለማድረግ ቢያቅዱና ቢያድሙም ምንም አይሳካላቸውም። 12 ፍላጻዎችህን በእነርሱ ላይ ታነጣጥራለህ፤ ወደ ኋላም ተመልሰው እንዲሸሹ ታደርጋለህ። 13 እግዚአብሔር ሆይ! ልዕልናህ ከፍ ከፍ ይበል፤ ስለ ታላቁ ኀይልህም የምስጋና መዝሙር እናቀርባለን። |