Biblia Todo Logo
የመስመር ላይ መጽሐፍ ቅዱስ
- ማስታወቂያዎች -

መዝሙር 147 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ለሁሉን ቻዩ አምላክ የሚቀርብ ምስጋና

1 እግዚአብሔርን አመስግኑ! ለአምላካችን የምስጋና መዝሙር ማቅረብ መልካም ነው፤ እርሱን ማመስገን ደስ የሚያሰኝና ተገቢ ነው።

2 እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ያድሳል፤ ከእስራኤል የተሰደዱትንም ይመልሳል።

3 ልባቸው የተሰበረባቸውን ይፈውሳል፤ ቊስላቸውንም ይጠግናል።

4 የከዋክብትን ብዛት ቈጥሮ ያውቃል፤ እያንዳንዳቸውንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።

5 አምላካችን ታላቅና ኀያል ነው፤ ለዕውቀቱም ወሰን የለውም።

6 ትሑታንን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ክፉ አድራጊዎችን ግን በምድር ላይ ጥሎ ያዋርዳቸዋል።

7 ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙር ዘምሩ፤ በገና እየደረደራችሁ ለአምላካችን ዘምሩ።

8 እርሱ ደመናን በሰማይ ላይ ይዘረጋል፤ ለምድር ዝናብን ይሰጣል፤ ተራራዎችንም በለምለም ሣር ይሸፍናል።

9 ለእንስሶች ምግብን ይሰጣል፤ ምግብ አጥተው የሚጮኹ የቊራ ጫጩቶችንም ይመግባል።

10 የእርሱ ደስታ በብርቱ ፈረሶችና፤ በጦረኞች ኀይል አይደለም።

11 እርሱን ደስ የሚያሰኙት በአክብሮት የሚፈሩትና በዘለዓለማዊ ፍቅሩ የሚታመኑ ሰዎች ናቸው።

12 ኢየሩሳሌም ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ! ጽዮን ሆይ! አምላክሽን አመስግኚ!

13 እርሱ የበሮችሽን መወርወሪያ አጠንክሮ ይጠብቃል፤ በውስጥሽ ያሉትንም ሕዝቦችሽን ይባርካል።

14 እርሱ ወሰንሽን በሰላም ይጠብቃል፤ በመልካም ስንዴም ያጠግብሻል።

15 ለምድር ትእዛዙን ያስተላልፋል፤ ቃሉም ወዲያው ይፈጸማል።

16 ዐመዳዩን እንደ ባዘቶ ያነጥፈዋል፤ ውርጩንም እንደ ዐመድ ይበትነዋል።

17 በረዶውንም እንደ ጠጠር አድርጎ ያወርደዋል፤ እርሱ የሚልከውን ውርጭ ማንም ሊቋቋመው አይችልም።

18 ከዚህ በኋላ ትእዛዝ ይሰጣል፤ የተጋገረውም በረዶ ይቀልጣል፤ ነፋስን ያነፍሳል፤ ውሃም ይፈስሳል።

19 ቃሉን ለያዕቆብ ልጆች ሕጉንና ሥርዓቱንም ለእስራኤል ይሰጣል።

20 ይህን ሁሉ ለሌሎች ሕዝቦች አላደረገም፤ እነርሱ ሕጉንም አያውቁም። እግዚአብሔር ይመስገን!

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
ተከተሉን:



ማስታወቂያዎች